ለፋሲካ እና ለኢድ በአላት ተጨማሪ ዘይት ከውጭ ሊገባ ነው፡፡


የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በመንግስት ትእዛዝ መሰረት የተገዛው 10ሚሊዮን ሊትር ተጨማሪ ዘይት ለአዲስ አበባ እና ለክልሎች ሊያሰራጭ ነው ፡፡
የንግድ እና የቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ እጥረት እንዳይፈጠር መንግስት የቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል ሲል አስታውቋል፡፡


የንግድ እና የቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ ሀሰን ሞሃመድ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት ከዚህ በፊት ከታዘዘው 40ሚሊዮን ሊትር ዘይት በተጨማሪ በቅርቡ በንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት የተገዛው ዘይት ጅቡቲ ወደብ ላይ የደረሰ በመሆኑ ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባቱና የማሰራጨቱ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በኮርፖሬሽኑ አማካኝነት የተገዛው 2.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለህብረተሰቡ መሰራጨቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስራ ላይ የሚገኙ 13 ያህል የዘይት ፋብሪካዎች የሚገኙ ቢሆንም ምርታማነታቸው ከ45 በመቶ አይበልጥም ተብሏል፡፡
አንድ ኢትዮጵያዊ በአማካኝ በወር እስከ 0.74 ሊትር ዘይት እንደሚጠቀም የሚኒስትር መስራቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡ይህም ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እንደሆነም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የነገሩን፡፡

በኢትዮጵያ በየወሩ እስከ 75ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንደሚያስፈልግም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ አመታዊ የዘይት ፍላጎቷን ለሟሟት 900 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንደሚያስፈልጋት ነው ሚኒስትር ዴኤታው ሀሰን ሞሃመድ ለኢትዮ ኤፍ ኤም የተናገሩት፡፡

ሚያዝያ 07 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.