የጃኖ ባንክ አክሲዮን ማህበር አደራጆች ቢሮውን ለቀው ጠፉ መባሉ ስህተት መሆኑን አደራጆቹ ለጣቢያችን አስረድተዋል፡፡

በምስረታ ሂደት ላይ የሚገኘው ጃኖ ባንክ ፣አደራጆች ቢሮውን ለቀው ጠፉ መባሉ ስህተት መሆኑንና ቅሬታም እንደፈጠረባቸው አደራጆቹ ለጣቢያችን ነግረውናል፡፡

አደራጆቹ እንደሚሉት ‹ቦሌ መድሃኒአለም አካባቢ የሚገኘው ቢሮችንን የለቀቅነው ለስራችን ምቹ የሆነ በታ ፈልገን ነው፣ አዲሱን ቢሮም ወደ ካሳንቺስ አካባቢ ለመቀየር የኪራይ ውል ስምምነት ለመፈጸም በሂደት ላይ ነን እንጂ ጠፍተን አይደለንም ብለውናል፡፡

በመቋቋም ላይ የነበረው ጃኖ ባንክም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዲስ መመሪያ አዲስ ባንክ ለማቋቋም የሚያችለውን አነስተኛ የመመሥረቻ ካፒታል ቀድሞ ከነበረበት 500 መቶ ሚሊዮን ብር ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉን ተከትሎ የባንክ ምሥረታ ሒደቱን ከመግታት ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው አማራጭ መሠረት ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ለመቀየር 2/3ኛውን የባለአክሲዮኖች ድጋፍ አግኝቶ እና ስምምነታቸውን በፊርማቸው አረጋግጦ ለብሔራዊ ባንክ ፊርማውን አስገብቷል ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክም የባለአክሲዮኖችን በዝግ አካውንት የሚገኝ ካፒታል ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋሙ አካውንት ለማዛወር በሒደት ላይ ይገኛል ብለውናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ቀደም ሲል ጃኖ ባንክ በምሥረታ ላይ፣ ሲገለገልበት የቆየውን ቦሌ መድኃኒዓለም ሞል የሚገኘውን ቢሮ የቀየረ በመሆኑ ይህንኑ መረጃ ባለመገንዘብ “አደራጆች ቢሮ ዘግተው ጠፉ” የሚል ዜና በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት መሰራጨቱን፣ ሌሎች ሚዲያዎችም ይህንን ያልተጣራ መረጃ ማንፀባረቃቸው ትክክል አይደለም ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የባለ አክሲዮኖች ካፒታል በዝግ አካውንት የተቀመጠ መሆኑን አንስተው ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ውጭ ፣ ማንም እንደፈለገ ሊያንቀሳቅሰው የማይችል በመሆኑ ባለአክሲዮኖች ካፒታሌ ይመለስልኝ የሚል ጥያቄ ካላቸው በሕጋዊ መንገድ ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል፡፡
ነገር ግን በአንዳንድ ሚዲያዎች ትክክል ያልሆነ መረጃ ከመስማታችን በቀር እኛ ጋር የቀረበ ቅሬታ የለም ሲሉ ለኢቲዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ሚያዝያ 07 ቀን 2014 ዓ.ም
ረድኤት ገበየሁ

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *