ለሚፈጠረዉ የጸጥታ ችግር ዋስትና ያጡ የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች በስጋት ከተማዋን ለቀዉ እየወጡ ነዉ ተባለ፡፡

የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ከከተማዋ ለመዉጣት ተገደዱት ሸዋሮቢት አካባቢ የተፈጠረዉ የጸጥታ ችግር ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋት ነዉ፡፡

የከተማዋ ከንቲባ አቶ አሳልፍ ደርቤ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ በአጣዬ ከተማ ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ጥቃት የተፈጸመ በመሆኑ ነዋሪዉ በቀላሉ ስጋት ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል ብለዉናል፡፡

እስካሁን በከተማዋ የተፈጠረ ነገር ባይኖርም፣ ቀደም ሲል ሲፈጸም ከነበረዉ ተደጋሚ ጥቃት አንጻር፣ ቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ገጠር ቤተሰቦቻቸዉ እየሄዱ ነዉ ብለዉናል፡፡

የቻልነዉን ያህል ለማረጋጋት እየሞከርን ነዉ ያሉት ከንቲባዉ፣ ሙሉ በሙሉ ምንም አትሆኑም፣ችገህርም አይፈጠርም ብለን ዋስትና ሰጥተን ከተማዋን እንዳይለቁ ለማድረግ ግን ተቸግረናል ነዉ ያሉት፡፡

ከከተማዋ የጸጥታ መዋቅር፣የክልሉ ልዩ ሃይላል የፌደራል ፖሊስ ጋር በጋራ እየሰራን ነዉ ያሉት አቶ አሳልፍ እስካሁን ሸዋሮቢት አካባቢ ከሚሰማዉ ችግር በስተቀር አጣዬ አካባቢ የተለዬ ነገር እንደሌለ አረጋግጠዉልናል፡፡

ከዚህ ቀደም ነዋሪዉ ከከተማ እንዳይፈናቀል አረጋግተን የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ግን የሰዉ ህይወት ሲጠፋና ንብረት ሲወደም ምንም ማድረግ አለመቻላችን አሁን ሙሉ ዋስትና ለመስጠት ተቸግረናል ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሸዋሮቢት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከ2ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ

ሚያዚያ 11 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.