ግጭትም ጥቃትም ያፈጠጠባት የሸዋሮቢት ከተማ አሁናዊ ሁኔታዋ ምን ይመስላል?

ኢትዮ ኤፍ ኤም ከሸዋሮቢት ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለዉ በስልክ እንዳረጋገጠዉ በአሁኑ ወቅት ከተማዋና አካባቢዉ ላይ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡
የክልሉ ልዩ ሃይልም ግጭት የነበረበት አካባቢ ላይ እንዲሰማራ ተደርጓል፤በዚህም አሁን በአካባቢዉ የሰላም አየር ነፍሷል ብለዋል፡፡

ግጭቱን በመሸሽ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተንቀሳቅሰዉ የነበሩ ሰዎችም ወደ ቀያቸዉ በመመለስ ላይ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
ለበዓሉ የሚሆኑ ግብይቶችም መከናወን መጀመራቸዉን ነግረዉናል፡፡

በግጭቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረዉ የትራንስፖርት አገልግሎት ከትናንት ረፋድ 5፡00 አንስቶ እንቅስቃሴ ጀምሯል፤እናም አሁን ባለዉ ሁኔታ በዓልን በሰላም ለማሳለፍ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል ብለዉናል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን በቀጣይ ጠንካራ ስራን ይጠብቃል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢዉ የሚደርሱ ጥቃቶችና ግጭቶች ተበራክተዋል፤እናም ጊዜያዊ መፍትሄ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፣ይህ ደግሞ ሰላምና ጸጥታን የሚያዉኩ አካላትን በግልጽ መለየትና ድጋሚ የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት መጠበቅ የሚያስችል ስራን ይጠይቃል፤አሁንም እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በግጭቱ የደረሰዉ ጉዳት ምን ያክል ነዉ በሚል ለቀረበላቸዉ ጥያቄ፣ በሰዉም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰዉን ጉዳት አሁን በግልጽ ለመናገር ጊዜዉ ገና ነዉ፤አጣርተን እናሳዉቃለን የሚል ምላሽ ሰጥተዉናል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ

ሚያዚያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *