ለ 72 ሺህ ተፈናቃዮች 400 የመጠለያ ድንኳን ጠይቃ 30 ድንኳን የተላከላት ዋግህምራ

ለ 72 ሺህ ተፈናቃዮች 400 የመጠለያ ድንኳን ጠይቃ 30 ድንኳን የተላከላት ዋግህምራ መጪው ክረምት አስግቷታል፡፡

ሰባ ሁለት ሺህ ተፈናቃዮችን ለማስተናገድ በትንሹ 400 ድንኳን ያስፈልገኛል ሲል መንግስትን የጠየቀው የዋግ ኽምራ ዞን ሶስት ሺህ ተፈናቃይ ብቻ ማስተናገድ የሚችል 30 ድንኳን ተልኮለታል

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን፣ በላስታ ላሊበላ እንዲሁም በትግራይ ክልል ድንበር በሚገኙ የዋግ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰባ ሁለት ሺህ ሰዎች በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ተፈናቅለዋል፡፡
የዞኑ ምግብ ዋስትና ከዚህ በፊት መንግስትን ወደ 400 ድንኳን እንደሚያስፈልገዉ ጠይቆ የነበር ቢሆንም የመጣለት ግን 30 ድንኳን ብቻ መሆኑን የዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ከፍያለዉ ደባሱ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡

አቶ ከፍያለዉ ደባሱ ለጣቢያችን እንደተናገሩት፤ ካሉት ሰባ ሁለት ሺህ ተፈናቃዮች ሶስት ሺዉ ብቻ ነዉ መጠለያ ያገኘዉ ያሉ ሲሆን ሌላዉ በግለሰብ ማዕድ ቤት ፣ በየመንገዱ ፣ በየፋብሪካዉ እንዲሁም ዝምብሎ ሜዳ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

‹‹የመጠለያ ችግር አልተፈታም ይሉቅንም እየባሰ ነዉ ››ያሉት አቶ ከፍያለዉ አዲስ የሚመጡ ተፈናቃዮች የምዝገባ ሂደቱ እስኪያልቅ ዝም ብለዉ በተለያየ ቦታ እንደሚቆዩ ተናግረዋል፡፡
መጪዉ የክረምት ግዜ ነዉ መጠለያ የሌለዉ ተፈናቃይ ደግሞ ምን ላይ ሊወድቅ እንደሚችል የታወቀ ነዉ የሚሉት የኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊዉ አቶ ከፍያለዉ መንግስት ይህንን ጉዳይ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል ሲሉም ያክላሉ፡፡

በመጪዉ የክረምት ግዜ አንድ ሁለቴ ዝናብ ከዘነበ ተፈናቃዮቹ ከፍተኛ የበሽታ ሁኔታ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ ከዞን ጤና መምሪያዎች ያገኘነው መረጃ ያሳያል ያሉት አቶ ከፍያለዉ በቅርቡም ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር እና በዞኑ ጤና መምሪያ በኩል ለመቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በሁሉም መጠለያ ጣቢያዎች ይህ ጉዳይ ከተከሰተ ለመቋቋምም ሆነ በሽታዉን ለመግታት በጣም ከባድ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
በቦታዉ በነበረዉ የህወሃት ሃይል ጤና ጣቢያዎች እና የተለያዩ የህክምና ማዕከላት በመዘረፋቸዉ እንደ ልብ መድሃኒቶችም ሆነ የህክምና ቁሳቁሶች ማግኘት ስለማይቻል ሁኔታዉን ከባድ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

አቶ ከፍያለዉ አክለዉም ከተፈናቃዮቹ ሌላ ማህበረሰቡም ቢሆን በምግብ ራሱን የቻለ ባለመሆኑ ችግሩን ከባድ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በአብዛኛዉ ትኩረታችን ተፈናቃዮቹ ላይ ሆኖ በመቆየቱና ዉስጥ ዉስጡን መመልከት ባለመቻላችን በረሀብ የሞቱ ሌሎች ሰዎች መኖራቸውን ልናረጋግጥ ችለናል ሲሉ አቶ ከፍያለዉ ገልጸዋል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.