የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን መልካ ጉባ ወረዳ ባደረገው ዘመቻ አካባቢውን ከሸኔ ታጣቂ ቡድን ነፃ ማድረጉን አስታወቀ።

በዚህ ዘመቻ በአካባቢው ለ4 አመታት ያህል በህዝቡ ላይ ስቃይ ሲያደርሱ ከነበሩ የቡድኑ ታጣቂዎች መካከል በርካታዎቹ መደምሰሳቸው ታውቋል።

የዕዙ የኋላ ደጀን አስተባባሪና የኦፕሬሽኑ መሪ ኮሎኔል ግርማ አየለ በዚህ ውጊያ ከ200 በላይ የሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን፣ ከ100 በላይ መቁሰላቸውንና 22 መማረካቸውን የገለፁ ሲሆን ከተደመሠሡት ውስጥም የአሸባሪው ህወሀት ታጣቂዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

መልካ ጉባ በተፈጥሮው በአስቸጋሪ የመሬት ገፅና ከፍተኛ የውሃ ሙላት ባለው ዳዋ ወንዝ መከበቡ፣ ሸኔን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮች በአካባቢው መገኘታቸው፣ ታጣቂ ቡድኑ ለአመታት በአካባቢው በመንቀሳቀስ ይዞታውን ማስፋቱ በዘመቻው የነበሩ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ ያሉት ኮሎኔል ግርማ ሰራዊቱ ሁሉንም ችግሮች እንደአመጣጣቸው በመመከት ድል ማስመዝገብ ችሏልም ብለዋል።

የዳዋ ወንዝ ከፍተኛ የውሃ ሙላትን እንደምሽግ በመጠቀም ለማጥቃት ሙከራ ያደረገውን የሸኔ ቡድንን ለመደምሰስ የሰራዊቱ ተነሳሽነት ከፍተኛ ነበር ያሉት ኮሎኔል ግርማ ዘመቻው የህይወት መስዋዕትነት ያልተከፈለበትና በጥንቃቄ የተመራ ተልዕኮ እንደነበርም ገልፀዋል።

ዘመቻው የጠላትን አንገት ያስደፋ፣ በርካታ የተዘረፉ ንብረቶችን ይዞ እንዳይወጣ ያደረገና ለአመታት ሰላም የጠማቸውን ህዝቦች የሰላም አየር የመለሰ ዘመቻ እንደነበርም ተናግረዋል።

ሽብርተኛው ሸኔ በቦታው በርካታ ዜጎችን በመግደል በጅምላ ቀብሯል ያሉት ኮሎኔል ግርማ መላው ህዝባችን የዚህን አረምኔ ቡድን መጥፎ ተግባር በመረዳት ልጆቹን ከዚህ ሽብርተኛ ቡድን ጥሪ እንዲጠብቅና መከላከያ ኃይሉን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

ሶስት ቀናትን በፈጀው ውጊያ ተማርከው እጃቸውን ከሰጡ የሸኔ አባላት መካከል ወጣት ጉዮ አዲ፣ ወጣት መሃመድ ረሽድ እና ወጣት ሰለሞን አምቢሳ እንዳሉት የሸኔ ታጣቂ ቡድን በተለያዩ የማደናገሪያ ስልቶች በመጠቀም ወጣቱን እየመለመለ የቡድኑ መጠቀሚያ ማድረጉን ይናገራሉ።

ቡድኑ የኦሮሞን ህዝብ ከመጨቆንና የኦሮሞን ህዝብ ከመግደል ያለፈ ምንም ፋይዳ የሌለው ስብስብ መሆኑን የተናገሩት ምርኮኞቹ የኦሮሞ ወጣት የዚህ ሽብርተኛ ቡድን መሰረተቢስ ዓላማ ተጋሪና ፈፃሚ መሆን የለበትም ሲሉ መናገራቸውን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ማህብራዊ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ፡- ኢ ፕ ድ

ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.