ከጠቅላላው የጤና ወጪ 82 በመቶው የሚሆነው ለመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚውል ተገለፀ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎት ምን ይመስላል የሚለው ላይ የተካሄደ የጥናት ውጤት ይፋ ሆኗል።

መርቅ ኮንሰልታንሲ በተመረጡ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች ያለውን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከአለም የጤና ድርጅት ጋር በትብብር የሰራውን ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል።

ጥናቱን በአራት የተለያዩ ክፍሎች በመከፋፈል እንደተሰራ የገለፁት ዶክተር አብሳላት ሰራዊት ፤ በፋይናንስ፣ በአቅም/ችሎታ ፣ በአፈፃፀም እና ተደራሽነት ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልፀዋል።

በፋይናንሱ ዘርፍ በቅርቡ ይፋ በሆነ የብሔራዊ የጤና ስሌት መሠረት፣ የጤና የነፍስ ወከፍ ወጪ እና በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች ላይ ያለው የጤና ወጪ ድርሻ በቅደም ተከተል 22 ዶላር እና 61 በመቶ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የገንዘብ ወጪ መንግስት 23 በመቶውን እንደሚሸፍንም ተነግሯል።

ሌላው ጥናት የተደረገበት ጉዳይ ተደራሽነት ሲሆን የተመቸ የጤና አገልግሎት የማግኘት ተደራሽነት ላይ እንቅፋት የሆነው የኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑ የተነሳ ሲሆን፣ ከተለያዩ የሀብት መጠን መለኪያዎች መካከል የተደረገው ንጽጽር እንደሚያመለክተው የ36 በመቶ ልዩነት አለ ተብሏል።
ከተደራሽነት አንፃር ሌላ የተነሳው ጉዳይ የእናቶች የትምህርት ደረጃ ሲሆን ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት እናቶች የሁለተኛ ደረጃ ወይም ከዚያ በላይ የተማሩ መሆናቸዉ ተነግሯል፡፡

በ2016 በተደረገ አንድ ጥናት በሳንባ ምች ከተያዙ ያልተማሩ እናቶች ካሏቸው ህፃናት መካከል 23 በመቶ የሚሆኑት እና ሁለተኛ ደረጃ እና ከዛ በላይ ደግሞ የተማሩ እናቶች ካሏቸው ህፃናት መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት ወደ ጤና ተቋማት መወሰዳቸውን እና ህክምና ማግኘታቸው ተገልጿል።
የተሻለ የትምህርት ደረጃ ያላቸው እናቶች የተሻለ የጤና ሁኔታ እንዳላቸውም በጥናቱ ተመላክቷል።

በእስከዳር ግርማ

ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *