ቶጎ ከሁለት አመታት በኋላ ድንበሯን ከፍታለች።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቶጎ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ይረዳ ዘንድ ከሁለት አመት በፊት ድንበሮቿን ከዘጋች በኋላ በትናንትናው ዕለት ድንበሯን እንደምትከፍት ተናግራለች።

ሀገሪቱ በዚህ ወር 32 የኮቪድ ታማሚዎችን ብቻ የመዘገበች ሲሆን፥ የሞተ ሰውም የለም።

“የ COVID-19 ጉዳዮች መቀዛቀዝን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም ድንበሮቻችን ይከፈታሉ” ሲል የቶጎ መንግስት በሰጠው መግለጫ ተናግሯል።

መንገደኞች የክትባት ማረጋገጫ እስካቀረቡ ድረስ ነፃ እንቅስቃሴ ሊቀጥል ይችላል ሲልም አክሏል።

የቶጎ ጎረቤቶች በሰሜን ቡርኪናፋሶ፣ በምዕራብ ጋና እና በምስራቅ ቤኒን ናቸው። በዚህም ባለሥልጣናቱ የመከላከያ እርምጃዎችን ማክበር መቀጥል አለብን ብለዋል ።
ባለፈው አመት መጋቢት ወር የጀመረው የክትባት ዘመቻም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መንግስት አስታውቋል።

በኤፕሪል መጨረሻ 32 በመቶ የሚሆኑት የሀገሪቱ ጎልማሶች ሙሉ በሙሉ መከተባቸው ታውቋል። የኮቪድ-19 ጉዳዮች በቁጥር እያሽቆለቆሉ በመምጣታቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቅርብ ወራት ውስጥ ርምጃዎች እንዲላሉ እየጠየቁ ነበር።

የቶጎ የመሬት እና የአየር ድንበሮች እ.ኤ.አ. በማርች 2020 የተዘጉ ቢሆንም የአየር ድንበሮች በዚያው አመት ነሐሴ ላይ እንደገና ተከፍተዋል። የባህር ድንበሮች ግን በጭራሽ አልተዘጉም።

ባለፈው ነሀሴ ወር አንዳንድ ወጣቶች ድንበሮች እንዲከፈቱ እና ንግድ እንዲቀጥል በመጠየቅ ከጋና ጋር በሚያዋስናቸው ድንበር ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል።
ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቶጎ 37,023 የኮቪድ ታማሚዎችን መዝግቧል ፣ ከእነዚህ ውስጥ 273 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው የኤ ኤፍ ፒ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *