‹‹እኛ ለትግራይ ህዝብ ለመድረስ የምዕራባዊያን ቡራኬም፣ አስገዳጅነትም፣ ጫናም ያስፈልገናል የሚል ዕምነት የለኝም የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ አካል ነዉ ህዝባችን ነዉ›› አቶ ክርስቲያን ታደለ

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የተለያዩ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ስለ ሰብዓዊ እርዳታ በተለያየ ግዜ የሀገራችንን መልካም ገጽታ በሚያጎድፍ ሁኔታ ሲያነሱ ይታያል፤ ነገር ግን እኛ ለትግራይ ህዝብ ለመድረስ የምዕራባዊያን ቡራኬም፣ አስገዳጅነትም፣ ጫናም ያስፈልገናል የሚል ዕምነት የለኝም የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ አካል ነዉ ህዝባችን ነዉ ሲሉ ለዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰብዓዊ እርዳታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

መንግስት መሰረታዊ በሆነ መንገድ ለትግራይ ህዝብም ሆነ አሸባሪዉ ህወሃት ላፈናቀላቸዉ የአፋር እና የአማራ ወገኖቻችን ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳያደርስ ዋነኛ ማነቆ የሆነበት ምንድነዉ? ሲሉ ጥያቄያቸዉን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን ያቀረቡት አቶ ክርስቲያን ታደለ ፤
‹‹ከተለምዷዊ የፖለቲካ ጫና ማሳደር ነዉ›› ከሚለዉ በዘለለ መንገድ መነሻዉ ምንድነዉ የሚለዉን ግለጽ የሆነ ማብራሪያ እንዲሰጠን እንፈልጋለን ሲሉም አክለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በሰጡት ምላሽም ፤የገባዉ ተሽከርካሪ እንዳይወጣ እየተደረገ ፣ለማድረስም የደህንነት ችግሮች እየተነሱ ከአቅም በላይ የሆኑ ጥያቄዎች ሲያስተጓጉሉን ቆይተዋል ፤ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ዉስጥ እንኳን ትግራይ ላሉ ተጎጂ ቤተሰቦች ዕርዳታ የማድረስ ሃላፊነት እና ግዴታ እንዳለብን እናዉቃለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በቅድሚያ በመንግስት በኩል የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረገዉ ለሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታዎችንን ለማመቻቸት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ይህ በተደረገ በሳምንታት ጊዜ ዉስጥ ግን ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ወረራ መካሄዱን አንስተዋል፡፡

‹‹ይህ ወረራ በተካሄደበት ሁኔታ፣ በየትኛዉም መልክ ወደ እዛ እርዳታ ለማስገባት ከአቅም በላይ ነዉ፤ በአየር መሰረታዊ የሚባሉ የመድሀኒት እና ቅድሚያ የሚሰጣቸዉ ጉዳዮችን ግን ለማድረስ ሞክረናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ከ1200 በላይ የዕርዳታ አቅርቦት የጫኑ መኪኖች ወደ መቀሌ ቢገቡም፣ እዛዉ መቅረታቸዉን አንስተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሰብዓዊ ዕርዳታዉን ማሰናከል ነዉ ያሉ ሲሆን፣ መኪኖቹ ከመቅረታቸዉ በላይ ለወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደዋሉም አክለዉ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ወደ ትግራይ የሚሄደዉን ዕርዳታ ያህል ወደ አፋርም መሄድ እንዳለበት እንደሚያምኑ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አማራ ክልል ረጅም ጊዜ በወራሪዉ ቁጥጥር ስር ዉሎ ስለነበር ዕርዳታዉን ለማድረስ አልተቻለም ብለዋል፡፡

እንደ ምክንያትም ወደ ክልሉ ለማስገባት እድሉ ቢገኝም ግን ስርጭቱን የሚያካሂዱ ተቋማት ቀድመዉ በትግራይ ክልል የዘረጉትን ስርዓት አይነት ለአማራ ክልል የተመቻቸ ስርዓት አለመዘርጋታቸዉን አንስተዋል፡፡

በአንድ በኩል በድርቅ ምክንያት የተጎዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች አሉን ፣በሌላ በኩል ጦርነቱ በተካሄደበት ቦታ ያሉ የምግብ ዋስትና ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች አሉ፤ ሙሉ ለሙሉ ተፈናቅለዉ የመጡ እንዲሁም በየቤቱ የሚገኙ ጦርነቱ ተጋላጭ ያደረጋቸዉ ሰዎች አሉ፤ስለዚህ ያለንን ሀብት ለዚህ ትኩረት በማድረግ ከዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ጋርም በመሆን እርዳታዉን የማፋጠን ስራ ነዉ የምንሰራዉ ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ለምክርቤቱ ወራሪዉ የህወሃት ሃይል ከአፋር ከወረዳ ማዕከላት እና ከተወሰኑ ወረዳዎች ወጥቷል እንጂ ዛሬም ድረስ በዚህ ወራሪ ሃይል ቁጥጥር ዉስጥ ያሉ ቀበሌዎች ስለመኖራቸዉም ተናግረዋል፡፡

እስከዳር ግርማ

ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *