የደህንነት ዕይታችን ሰፊ እና አካታች መሆን እንዳለበት የዉጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የጥናትና ምርምር ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጃፋር በድሩ ናቸዉ ለኢትዮ ኤፍኤም የተናገሩት፡፡
የዉጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት‹‹ የብሄራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ምንነት፣አቀራረጽና እና አስፈላጊነት›› በሚል ርዕስ የፖሊሲ ምክክር መድረክ በትናንትናዉ ዕለት አዘጋጅቶ ነበር፡፡
በዚህ መድረክ ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ በ1987 ዓ.ም የፌደራል ስርዓት ካዋቀረችበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ የተጻፈ እና ከዉጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጋር የተጣመረ የብሄራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ነበራት የተባለ ሲሆን፤
ይህ ስትራቴጂ በሀገራችን የመንግስት ለዉጥ እስከተካሄደበት 2010 ድረስ እንደዋነኛ የዉጭ ግንኙነትና የብሄራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱ ተገልጿል፡፡
የዉጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በአዲስ መልክ የተቀረጸና መሻሻል ተደርጎበት በመከለስ ላይ ያለ ቢሆንም፤ የሀገራችንን የብሄራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አስመልክቶ ከዚህ በፊት የነበረዉና አሁን ላይ በመከለስ ላይ ያለዉም ቢሆን ‹‹ከዉጭ የሚመጣን ስጋት መከላከል››በሚል ዉስን ሀሳብ እና ተግባር ላይ የተወሰነ መሆኑ ተነስቷል፡፡
በሀገራችን የነበረዉ የደህንነት አረዳድ በጣም ጠባብ ነበር የሚሉት አቶ ጃፋር ብሄራዊ ደህንነታችንን ከመንግስት፣ ከተቋማት እና ከስርዓት ደህንነት ዉጭ ለይቶ አያይም ነበር ብለዋል፡፡
ሌላዉ ደግሞ የደህንነት ስትራቴጂያችን አካታች አልነበረም ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሁሉም የደህንነት ተቋማት ተሳትፈዉበት፣ ችግራቸዉንም ለይተዉ የብሄራዊ ደህንነታችን ላይ አደጋ ሊደቅን የሚችለዉ ይህ ጉዳይ ነዉ የሚለዉን ተነጋግረዉበት የተቀረጸ አይደለም ሲሉ ያክላሉ፡፡
ስለዚህ የህዝቡ ደህንነት ከመንግስት ተቋማት እና የሀገርን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ጋር አብሮ ታሳቢ ተደርጎ ይህ ስትራቴጂ መቀረጽ አለበት ያሉ ሲሆን ፤ ደህንነት ሲባል ከበሽታ፣ ከወረርሺኝ ፣ከተፈጥሮ አደጋዎች፣ ከድህነት ህዝቡን መጠበቅ እንዲሁም ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስጠበቅንም ያካትታል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዉ ተናግረዋል፡፡
በእስከዳር ግርማ
ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም











