“የመዲናዋ ህንፃዎች ግራጫ ቀለም ይቀባሉ የሚል ዉሳኔ አልተላለፈም ተባለ፡፡

የአዲስ አበባ ህንፃዎች ሁሉ ግራጫ ቀለም ሊቀቡ ነው በሚል ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚናፈሰው መረጃ ከዕውነት የራቀ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ አስታዉቀዋል።

የቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት፤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የህንፃ ስታንዳርድና የውጭ ማስታወቂያ ስታንዳርድ እየተዘጋጀ ነው፡፡
ሆኖም ግን ይህን መነሻ አድርጎ በማህበራዊ ትስስር ገጾች አዲስ ከተማ ግራጫ ቀለም ልትቀባ ነው በሚል በስፋት ሲዘዋወር የታየው መረጃ የተሳሳተ ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ የከተማዋ ህንጻዎች ቀለም ምን አይነት ይሁን የሚለው ጉዳይ ለውይይት ቀረበ እንጂ የከተማ አስተዳደሩ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ውሳኔ እንዳላሳለፈ ለኢፕድ አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም ከዚህ ቀደም ‹‹ከተማችን ቡራቡሬ ሆና ባለቤት አልባ መስላለች›› ማለታቸውን ያስታወሱት የቢሮ ኃላፊው፤ ይህን ችግር ማንኛውም የመዲናዋ ነዋሪም ሊታዘብ ይችላል። የከተማ አስተዳደሩም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት የውጭ ማስታወቂያውና የከተማዋ ቀለም ሁኔታ የሚመራበት ስታንዳርድ ዝግጅት ተደረገ እንጂ ውሳኔ ላይ አለመድረሱን ጠቁመዋል።
በቅርቡ በጉዳዩ ላይ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ ይህን መነሻ አድርገው አንዳንድ ግለሰቦች ለግራጫ ቀለም የመሰላ ቸውን ትርጓሜ ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ ጉዳዩ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንደሚዘዋወረው ተግባር ላይ የዋለ ሳይሆን ገና ለምክክር የቀረበ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ከተማዋ ላይ አንድ አይነት ቀለም ብቻ ለቀለም ቅብ ሥራ ያስፈልጋል የሚል እሳቤ መያዝ እንደሌለበት የተናገሩት ኃላፊ፤ ለአስፈላጊው ህንጻና አካባቢ የሚመጥን ዝብርቅርቅ ያልሆነና ለዓይን የሚማርኩ ቀለማትን የያዘ ስታንዳርድ እንደሚኖረን ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።

የከተማዋ ቀለም ስታንዳርዱን የጠበቀ መሆን አለበት የሚለው ሀሳብ ሁላችንንም ሊያስማማ የሚችል ጉዳይ ነው ያሉት ዮናስ ዘውዴ፤ የከተማው ነዋሪ ያልመከረበትና ስምምነት ላይ ያልደረሰበት ምንም ነገር ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.