ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በዓለምዓቀፍ ደረጃ ተፈናቅለዋል ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ባወጣዉ መረጃ መሰረት በዓለምዓቀፍ ደረጃ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በግዳጅ ተፈናቅለዋል ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን በቅርቡ በሰበሰበዉ አዲስ መረጃ መሰረት ጥቃትን፣ ግጭትን፣ ግድያን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመሸሽ መኖሪያ ቀያቸዉን ለቀዉ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከ100ሚሊዮን በላይ ነዉ ብሏል፡፡

ብዙ ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ ቀያቸዉን ጥለዉ እንዲሸሹ ካደረጋቸዉ የመጀመሪያዉ ምክንያት በዩክሬን ያለዉ ጦርነት መሆኑን የገለጸዉ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ እና ኮንጎ ለረጅም ግዜ የቀጠለዉ የዕርስ በዕርስ ግጭት ለዚህ ቁጥር መጨመር የራሳቸዉ ሚና እንደነበራቸዉ አክሎ ገልጿል፡፡

‹‹በፍጹም ልናየዉ የሚገባ ቁጥር አልነበረም›› ሲሉ የኮሚሽኑ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተፈጠሩ እና ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ አዉዳሚ ግጭቶችን ፣ ግድያዎችን ለማስቆም ይህ የማንቂያ ደዉል መሆን አለበት ያሉ ሲሆን ከዚህ በኋላ ንጹሃን ዜጎች ቤታቸዉን ለቀዉ እንዳይሰደዱ ችግሩን ከስሩ መፍታት›› አለብን ብለዋል፡፡
የተሰበሰበዉ መረጃ ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን ያካተተ ነዉ፡፡ባለፈዉ ሳምንት በወጣ መረጃ መሰረት የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 60ሚሊዮን መድረሱም ነዉ የተገለጸዉ፡፡

ኮሚሽነሩ የመፈናቀል እና የመሰደድ ምክንያቶችን ከስራቸዉ ነዉ መለየት ያለብን ምክንያቱም የሰብዓዊ እርዳታዎች ለግዜዉ ችግሩን ማከም ብቻ ነዉ ስራቸዉ ሲሉ ተናገረዋል፡፡
አክለዉም ንጹሀን ዜጎች በሀገራቸዉ ባለዉ ግጭት እና ሀገራቸዉን ጥለዉ በመሰደድ አጣብቂኝ ዉስጥ እንዳይወድቁ ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ ብቸኛዉ ምላሽ ሊሆን የሚችለዉ ሰላም እና ደህንነት ነዉ ሲሉ ለሮይተርስ ገልጸዋል፡፡

እስከዳር ግርማ

ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.