በሱዳን በፀረ መፈንቅለ-መንግስት ተቃውሞ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 98 መድረሱ ተሰምቷል።

ከጥቅምት 25 ቀን 2014 ጀምሮ በጦር ኃይሎች አዛዥ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የሚመራውን ወታደራዊ አገዛዝ ተከትሎ በተካሄደው የፀረ መፈንቅለ መንግስት ተቃውሞ ላይ በተወሰደው እርምጃ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 98 መድረሱ ተገልጿል::

የህክምና ባለሙያዎች እንደገለፁት፣ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በመቃወም የወጡ ሁለት ተቃዋሚዎችን፣ የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች መግደላቸዉንና ይህም የሟቾችን ቁጥር ወደ 98 ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ዶክተሮቹ እንደሚሉት በዋና ከተማዋ ካርቱም ውስጥ በተደረጉ ሰልፎች ላይ አንድ ተቃዋሚን በጥይት ከመቱት በኋላ ህይወቱ ማለፉን እና ሌላው በአስለቃሽ ጭስ ታፍኖ መሞቱን አስታውቀዋል።

እ.ኤ.አ.በ2019 ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ለሶስት አስርት አመታት የዘለቀው አገዛዝ ላይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች መነሳታቸውን ተከትሎ በተካሄደ መፈንቅለ መንግስት ወደ ሲቪል አገዛዝ የሚደረገው ሽግግር እንዲጠናከር አድርጎታል።
ሱዳን በአልበሽር አስተዳደር ስር በነበረችበት ወቅት፣ ዓለም አቀፍ መገለል የደረሰባት ሲሆን፣ በተጨማሪም የመልካም አስተዳደር እጦት እና ለአስርት አመታት የዘለቀው ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ሲያናጋት ቆይቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአፍሪካ ህብረት እና ከኢጋድ ጋር በመሆን ቀውሱን ለመፍታት በሱዳን መንግስት የሚመራ ውይይት እንዲመቻች ግፊት ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ነገር ግን የሲቪል ሃይሎች ከጦር ኃይሉ ጋር ወደ ድርድር ለመግባት ፈቃደኛ አልሆኑም፣በዚህም አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የተባበሩት መንግስታት ተወካይ ቮልከር ፔርቴስን በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ “ጣልቃ ገብቷል” በማለት በተደጋጋሚ ሲከሱ ነበር ።

ሱዳን ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ በአለም አቀፍ ደረጃ ይደረግ የነበረው ዕርዳታ በመቀነሱ ከባድ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ / AFP/ዘግቧል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *