በአራዳ ክፍለ ከተማ “ቀይ ኮከብ” አፀደ ህፃናት እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከሰተው ምንድን ነው?

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓም ከምሳ ሰአት በኋላ ለሚኖረው የትምህርት ክፍለ ጊዜ የተዘጋጁ ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በአካባቢው ነዋሪ የሆነ አንድ ወጣት ተማሪዎች ‹‹ሰድበውኛል›› በሚል ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በመግባት 4 ወለሎች ያሉትን ህንፃ በመውጣት የ9ተኛ ክፈል ተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈፅሟል፡፡
ግለሰቡ ይዞት በነበረው መዶሻ በተማሪዎች ላይ የተለያየ አይነት ጉዳት አድርሶባቸዋል፡፡

ይህ ሲሆን የትምህርት ቤቱ ጥበቃ ሰራተኞች ግለሰቡን ማስቆምም ሆነ ተማሪዎችን ከጉዳት መታደግ አልቻሉም ነበር፡፡
ጉዳዩን ሊያረግበው የቻለው የፖሊስ አካባቢው ላይ መድረስ ቢሆንም፣ በድጋሚ ግለሰቡ ቅጥር ግቢ ውስጥ መግባት ችሎም እንደነበር ሰምተናል፡፡

ከተማሪዎቹ መካከል ጭንቅላታቸውን የተመቱ፤ እግራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው እና በጣም የተረበሹ ተማሪዎችን ማክሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በቦታው ተገኝተን ተመልክተናል፡፡
እንደ ትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ከሆነ 3 ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉ ቢሆንም፣ ወላጆች ደግሞ ከ15 ያላነሱ ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለውናል፡፡

ጉዳት አድራሹ ግለሰብ ‹‹የአእምሮ ህመምተኛ እና የእፅ ተጠቃሚ ነው›› ሲሉ ወላጆች እና የትምህረት ቤቱ ርእሰ-መምህር የነገሩን ቢሆንም ማረጋገጥ ግን አልቻልንም፡፡

ፖሊስ ከክስተቱ በኋላ ለትምህርት ቤቱ የተጠናከረ ጥበቃ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን ምርመራው መቀጠሉንም ሰምተናል፡፡
በትምህርት ቤቱ በር አካባቢ ላይ የሲጋራ እና የጫት ቁርጥራጮችን በቦታው ተገኝተን የተመለከትን ሲሆን ‹‹ እንዴት የትምህርት ተቋም አቅራቢያ ›› ይህ ይደረጋል የሚል ጥያቄ ለወረዳ 2 አስተዳደር ያቀረብን ሲሆን ምላሽ እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡

እንዲህ አይነት ክሰተቶችም አሉና ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነዉ፡፡

በአብዱሰላም አንሳር
ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *