ሦስተኛው ዙር የህዳሴው ግድብ ሙሌት በሐምሌ ወር እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡
የሁለተኛው ተርባይን ፍተሻም ተጀምሯል ተብሏል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ ሦስት ወራት ያለፉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት፣ ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ መከናወን እንደሚጀምር ታዉቋል፡፡

ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ ወደ ግድቡ የሚፈሰው የውኃ መጠን፣ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ከፍ እያለ ከሄደ በኋላ ወደ ግድቡ የሚገባውን ውኃ በመያዝ፣ በሐምሌ ወር ሙሌቱ እንደሚጀመር ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመት ወደ ግድቡ እንዲገባ የሚጠበቀውን የውኃ መጠን ለመያዝ የግድቡን ቁመት የመጨመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ የውኃ ሙሌቱ ሲጀመር የግድቡ ቁመት በሚፈለገው መጠን እንደሚደርስ አስረድተዋል፡፡

ከክረምቱ መግባት በኋላ ባሉት ወራት የሚኖረው የውኃ መጠን የሚለያይና እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ፣ ከፍተኛው የውኃ መጠን የሚታየው በነሐሴ ወር ነው ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከሐምሌ ጀምሮ የሚፈለገው የውኃ መጠን ተይዞ፣ በነሐሴ ወር ውኃው በግድቡ ላይ ይፈሳል ሲሉ ያላቸዉን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.