ታይላንዳዊዉ ግለሰብ ለድንገተኛ ቀዶ ጥገና ወደ ሆስፒታል የገባዉ እሾሃማ የሆነ አሳ ከዉሃ ዉስጥ በመዉጣት በቀጥታ ወደ ግለሰቡ የተከፈተ አፍ በመግባት ጉሮሮዉን በመንከሱ ነዉ፡፡
ጉዳዩ ‹‹የጅሎች የኮሜዲ ፊልም›› ሊመስል ይችላል የሚለዉ ኦዲቲ ሴንትራል፣ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕዉቅናን ያገኙ የታይላንድ መገናኛ ብዙሀን ፣ ከዉሃ ዉስጥ ድንገት ዘሎ የወጣ ትንሽ አሳ በአጥማጁ የተከፈተ አፍ ዉስጥ ገብቶ ጎሮሮዉ ላይ ተሰንቅሮ አንቆ ሊገለዉ እንደነበር ዘግበዋል፡፡
ስሙ ያልተቀሰዉ ይህ ግለሰብ በወንዙ አሳ በማጥመድ ላይ ነበር የተባለ ሲሆን፣ በመሀልም ለመተንፈስ አፉን በሚከፍትበት ወቅት ከየት መጣ ያልተባለ ትንሽ አሳ በድንገት ከዉሃዉ ዉስጥ በመዉጣት ዘሎ ጉሮሮዉን በመንከስ ለመተንፈስ እንዳይችል አድርጎታል ተብሏል፡፡
ይህ አስደንጋጭ ክስተት የአሳ አጥማጁን ህይወት ሊነጥቀዉ እንደነበር ተገልጿል፡፡ አሳ አጥማጁ ለመተንፈስ በጣም ተቸግሮ ሲንፈራገጥ ያዩት በአቅራቢያዉ የነበሩ ሰዎች፣ የተፈጠረ ችግር መኖሩ ገብቷቸዉ ሊደርሱለት እና ወደ ሆስፒታልም ይዘዉት መሄዳቸዉ ነዉ የተገለጸዉ፡፡
የዶክተሮች ቡድን አንድ ሰዓት በፈጀ የቀዶ ጥገና ስራ በደም የተጨማለቀዉን አሳ ከግለሰቡ ጉሮሮ ማዉጣታቸዉን እና ግለሰቡ ሙሉ በሙሉ ድኖ ከሆስፒታሉ መዉጣቱም ተነግሯል፡፡
‹‹እንደዚህ አይነት ነገር የመከሰቱ ዕድል በጣም ዝቅተኛ ነዉ፣ ከዚህ በፊት በፍጹም እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞኝ አያዉቅም›› ያሉት ዶክተሩ ፣ ‹‹ሀኪሞቻችን ታካሚያችንን ለማዳን እና በጉሮሮዉ ላይ የሚደርሰዉን ጉዳትም ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ፣ ተሳክቶላቸዋልም›› ሲሉ አክለዋል፡፡
በህይወት ባለ አሳ ጉሮሮን መነከስ ምናልባትም አስደሳች ክስተት አይደለም፡፡ በእርግጠኝነትም አንገት ላይ በጩቤ ከመወጋት በላይ ከባድ ስሜት ይኖረዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘገባዉን አጠቃሏል፡፡
በእስከዳር ግርማ
ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም











