አሳዛኙ የትራፊክ አደጋ በጉራጌ ዞን!

በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ መንገድ ስቶ ወደ ሰው ቤት የገባው ተሸከርካሪ ሁለት ህጻናት በተኙበት ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል፡፡

በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ አዶሼና አቱርቸ ቀበሌ ልዩ ስሙ “አሞራ ሜዳ “በሚባል ቦታ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ህፃናት ህይወት ማለፉን የቸሃ ወረዳ ፖሊስ አስታውቋል።

አደጋው የደረሰው ከሆሳዕና ወደ ወልቂጤ በሚወስደው መስመር አረቅጥ ከተማ ገረጋንቲ አራግፎ ሲመለስ የነበረ ገልባጭ መኪና የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኢት 33832 መንገድ ስቶ በመውጣቱ ነው ተብሏል።

የቸሀ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ገና ደገሙ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደገለፁት፣ ተሽከርካሪው መንገድ ስቶ በመውጣት ምክንያት የአቶ ሀሰን ዱላ መኖሪያ ቤት ውስጥ በመግባት በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

በአደጋው ቤት ውስጥ የነበሩ ሶስት ህፃናት ላይ አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን የስምንት አመት ሴት ልጅና የአራት አመት ወንድ ልጅ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል እንደደረሱ ህይወታቸው ሲያልፍ አንዱ ህፃን በወልቂጤ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና ላይ እንደሚገኝና መኖሪያ ቤቱም ከነ ንብረቱ መውደሙን ገልፀዋል፡፡

አሽከርካሪውም ጉዳት ደርሶበት በህክምና ላይ እንደሚገኝ የፖሊስ አዛዡ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.