የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ አገራቸው የአባይ ውሃ ድርሻዋን ለማሳደግ ከአፍሪካ መንግስታት ጋር ግጭት ውስጥ እንደሌለች ትናንት እሁድ ገልጸዋል።
ፕሬዝደንት አል ሲሲ ይህን ያሉት ትላንት እሁድ በካይሮ በተጀመረ አንድ መድረክ ላይ ነው፡፡
“በአባይ ውሃ ውስጥ ያለን ድርሻ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ይደርሳል፣ የህዝቡ ቁጥር ሦስትና አራት ሚሊዮን ከነበረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ለውጥ አላመጣም” ሲሉ ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የጀመረችውን ሰላማዊ አካሄድ በማስመልከት መናገራቸውን አሻርክ አል አውሳት ዘግቧል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ግዙፉ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ነው፡፡
ካይሮ ግድቡን ለመሙላት እና ለመስራት ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ህጋዊ አስገዳጅ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥያቄዋን ደጋግማ ማቅረቧን ዘገባዉ ጠቁሟል፡፡
በሚያዚያ 2021 መጀመሪያ ላይ በኪንሻሳ በተካሄደው የሶስቱ ሀገራት የመጨረሻ ዙር ድርድር ምንም መሻሻል ሳይታይበት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
“ይህን የውሃ ድርሻ ለመጨመር ከአፍሪካ ወንድሞቻችን ጋር ግጭት ውስጥ አልገባንም” ሲሉ ፕሬዝደንት አል ሲሲ ተናግረዋል።
ግብፅ በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ለመግጠም ምንም ፍላጎት እንደሌላት ደጋግማ ትናገራለች ፡፡
ካይሮ በግድቡ ላይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ሰላማዊ የፖለቲካ መንገዶችን በመከተል ድርድሩ ለመቀጠል እንደምትሻም ተናግራለች፡፡
በግብፅ ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶ/ር ሳማ ሱሌይማን ለአሻርክ አል አውሳት እንደተናገሩት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋዊ መግለጫዎች ግብፅ በግድቡ ላይ አለም አቀፍ ህግጋትን በተከተለ መልኩ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያላትን ፍላጎት ያሳያል ብለዋል።
በያይኔአበባ ሻምበል
ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም











