ሪያንኤር ደቡብ አፍሪካውያን መንገደኞች ከመጓዛቸው በፊት ማንነታቸዉን ለመለየት ቋንቋን እንደዜግነት ማረጋገጫ መጠቀሙ እያስተቸዉ ይገኛል፡፡

ደቡብ አፍሪካውያን የአይሪሽ አየር መንገድ ሪያንኤርን /Ryanair/ በእንግሊዝ በረራዎች ላይ የአፍሪካንስ ቋንቋ ችሎታቸውን በመፈተሽ ዜግነታቸውን እያረጋገጠ መሆኑ አግላይ ነው ሲሉ አውግዘዋል።

አፍሪካንስ በደቡብ አፍሪካ 12 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቷ ህዝብ ብቻ የሚጠቀምበት ቋንቋ ሲሆን፣ ከረጅም ጊዜ ጀምሮም ከአፓርታይድ እና አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ነጮች ጋር አብሮ ስሙ የሚነሳ ነው።
ሪያንኤር በበኩሉ ፈተናውን በተጭበረበረ የደቡብ አፍሪካ ፓስፖርት ለመጓዝ የሚሞክሩ አጭበርባሪዎችን ለመቆጣጠር እንደሚጠቅምበት በመግለጽ ይከራከራል፡፡

“ቁጥሩ እየጨመረ በመጣው በተጭበረበሩ የደቡብ አፍሪካ ፓስፖርቶች ወደ እንግሊዝ የመጓዝ ጉዳይን ለመቀነስ፣ ተሳፋሪዎች በአፍሪካንስ ቋንቋ የተዘጋጀ ቀላል መጠይቅ እንዲሞሉ እንፈልጋለን” ሲል በመግለጫው አሳውቋል።

አየር መንገዱ ተሳፋሪዎች መጠይቁን መሙላት ካልቻሉ፣ጉዟቸው ውድቅ እንደሚደረግ እና ሙሉ ገንዘባቸውም ተመላሽ እንደሚሆን ተናግሯል።

ሪያንኤር በአገልግሎት አቅርቦቱ ላይ ከደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን፣ከሌላ የአውሮፓ ክፍል ወደ እንግሊዝ የሚበር ማንኛውም የደቡብ አፍሪካ ፓስፖርት የያዘ ሰው ጉዳይም እንደሚመለከተው ገልጿል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት የእንግሊዝ ከፍተኛ ኮሚሽነር በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ፈተናው የእንግሊዝ መንግስት መስፈርት አይደለም ብለዋል።
የአየር መንገዱ አዲስ መስፈርት የደቡብ አፍሪካ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ዲፓርትመንት በቅርቡ ማንነትን በማጭበርበር እና የውሸት ፓስፖርቶችን በመፍጠር የሚሰሩ ወንጀለኞች ተበራክተዋል ሲል መቆየቱን ተከትሎ የወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ቋንቋው በአፓርታይድ ጊዜ በጥቁሮች ላይ በግድ ተጭኖ የነበረ በመሆኑ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ቋንቋውን የሚጠቀሙበት ባለመሆኑ፣ ደንበኞቹ ሪያንኤር ይህን ቃለመጠይቅ በማዘጋጀቱ የዘር መድልዎ ፈጽሟል በማለት ቅሬታቸዉን ማቅረባቸዉን ሲ ጂ ቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *