የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ195 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡

የገንዘብ ድጋፋ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባቶችን በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍና በግጭቶች የተጎዱ የህዝብ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋምም የሚረዳ ነው ተብሏል።

ወቅታዊው የገንዘብ ድጋፍ በጫና ውስጥ ላለው የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት አጋዥ ከመሆን በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከ30 በመቶ በታች ያለውን የኮቪድ-19 የክትባት ሽፋን ለማሳደግና በመላ አገሪቱ የክትባት ሥራዎችን በማስፋፋት የኮቪድ-19ን ስርጭትና ተጽእኖ ለመቀነስ ይረዳል ነዉ የተባለዉ።

በእናቶች እና ህጻናት ጤና አጠባበቅ ረገድ ፣በሥነ-ምግብ እና ሌሎች ቁልፍ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የገንዘብ ድጋፉ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና በግጭቱ የተጎዱ የገጠር አካባቢዎችን እና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመድረስ ብሎም ለኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ታዉቋል፡፡

በተጨማሪም ድጋፋ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ግዢ ለማድረግ ፣የሆስፒታል የፅኑ ህሙማን ክፍል (አይሲዩ) መሳሪያዎችን ለማሟላት ፣ በኮቪድ-19 እና በሌሎች ህመሞች ላይ ያሉ ህመምተኞችን አያያዝ የበለጠ ለማሻሻል እንዲሁም የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ይውላል ተብሏል።

የገንዘብ ድጋፋ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2023 መጨረሻ ለ60 በመቶ ዜጎች የኮቪድ-19 ክትባትን ለማዳረስ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ሲሆን፣ ይህ የ195 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ምላሽ የሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ከ495 ሚሊዮን ዶላር ያደረሰው መሆኑ ከገንዘብ ሚንስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.