በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የአገልግሎቱ ሚንስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በዛሬው እለት በሰጡት መረጃ በትግራይም ሆነ በሌሎች ክልሎች ላይ ከሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ጋር በተያያዘ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡
እሰከ ግንቦት 26 ተደርጓል ያሉትን ድጋፍ በተመለከተም በትግራይ ክልል በየብስ በኩል 86 ሺ 700 ሜትሪክ ቶን የምግብ ድጋፍ መደረጉን፤ በአየር ትራንስፓርት 216 ሺ ኪ.ግ መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ፤ እንዲሁም ባለፍት ሁለት ወራት ውስጥ 782 ሺ ሊትር ነዳጅ በየብስ በኩል ተደራሽ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በአማራ ክልል ሲደረግ የነበረውን ድጋፍ በተመለከተ በክልሉ 11 ሚለየን ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መቆየቱን አንስተው ለእነዚህም ዜጎች ከ775 ሺ በላይ ሜትሪክ ቶን የምግብ ድጋፍ ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የሰሜን ወሎና ዋግህምራ አካባቢም ለ128ሺህ ዜጎች 483 ሜትሪክ ቶን የምግብ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን በግጭት ለተፈናቀሉ 2 መቶ ሺ ዜጎች ከ 1 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ድጋፍ ተደርጓል ሲሉ የአገልግሎቱ ሚንስትር ዴኤታ ገልፀዋል፡፡
በአፋር ክልል ባሉ ማእከላት ውስጥ ለሚገኙ ለ 6 መቶ ሺ ዜጎች 19 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ ድጋፍ እንደተረገም ተገልጿል፡፡
በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከቤት ንብረታቸው የተፈናሉ ዜጎችን ለመመለስ በመንግስት በኩልም ሆነ ከዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ጋር እየተሰራ ቢሆንም ይህ በቂ እንዳልሆነና በህብረተሰቡና በመንግስት ከዚህ ቀደም ሲካሄዱ የነበሩት የድጋፍ ንቅናቄዎች እንደሚያስፈልጉም ተጠቁሟል፡፡
በየዉልሰዉ ገዝሙ
ሰኔ 03 ቀን 2014 ዓ.ም











