ቻይና የመጀመሪያውን የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ ልታካሂድ ነው።

ቻይና ከሰኔ 20 እስከ 21 ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንደምታዘጋጅ ገልጻለች።

ቻይና በዚህ አመት በየካቲት ወር አንጋፋውን ዲፕሎማት ዙ ቢንግን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ከሾመች በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያው የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ኮንፈረንስ ይሆናል ተብሏል፡፡

ልዩ መልዕክተኛ ዙ ቢንግ ባለፈው መጋቢት ወር ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፣ ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የደህንነት፣ የልማት እና የአስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እና አንድነትን ለማጎልበት አብራ ትሰራለች፡፡

ለዚህ ደግሞ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የቀጣናው ወሳኝ ሀገር በመሆኗ ሰላምን በማስፈን ረገድ ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባት አስምረውበታል” ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ደቡብ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት እንደዘገበው በሱዳን የቻይና አምባሳደር ማ ሺንሚን ከሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበታች ሴክሬታሪ ናዲር ዩሲፍ አል ታዬብ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ኮንፈረንሱ ልማትን እና መረጋጋትን ለማሳደግ ከቻይና የመጣ ተነሳሽነት ነው ብለዋል።

በዚህ አስፈላጊ ክልል ውስጥ መልካም አስተዳደር ለመገንባት ወሳኝም ነው ” ሲሉም አክለዋል፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በያዝነው አመት ጥር ወር ላይ በኬንያ ባደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳንን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ባለው ግጭቶች እና አለመረጋጋት ቻይና በምስራቅ አፍሪካ የምታደርገውን ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች ስጋት ውስጥ እንደጣላቸው ተናግረዋል፡፡

እናም ቻይና በቀጠናው የሰላም ኮንፈረንስ ማስተዋወቅ ትፈልጋለች ሲሉ ገልጠዋል።

በያይኔአበባ ሻምበል

ሰኔ 03 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *