የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተወሰዱ ቁልፍ የመተማመን እርምጃዎችን በደስታ እንደተቀበሉት ገለጹ::

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪቃ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የናጂሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴን ኦባሳንጆ በአፍሪካ ቀንድ የተሰጣቸውን ተልእኮ አፈፃፀም በተመለከተ ስላደረጉት ቆይታ ገለፃ አድርገውላቸዋል።

ሊቀመንበሩ በተለይ በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ አካላት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኝነትን የገለጹት ሀገራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት፣ የታሰሩትንና የጦር እስረኞችን በመፍታት፣ ግጭቶችን በማቆም በመሆኑ ይህ ጉልህ የመተማመን ግንባታ እርምጃዎች ናቸው ብለዋል።

ብሔራዊ የውይይት ኮሚሽን፣ የሰብአዊ እርቅና የተኩስ አቁም አዋጅ፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከአፋር ክልል መውጣት ከጠቀሷቸው በጎ ጅምሮች ውስጥ ይገኙበታል።
ሊቀመንበሩ ሁለቱ ወገኖች የደረሱትን የሰብአዊ እርቅ እና የተኩስ አቁምን ተከትሎ ለተጎዱ ክልሎች የሚደረሰው የሰብአዊ አቅርቦት እና ድጋፍ መሻሻሎችን በደስታ እንደተቀበሉት አስታውቀዋል፡፡

ህብረቱ በይፋዊ ገጹ እንዳስነበበው እነዚህ እርምጃዎች በአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ በተደረጉ ጠንካራ ዲፕሎማሲዎች መሆናቸውን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
በዚህም አጠቃላይ ግጭቶችን እንዲቀንሱ ሆነዋል ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ሊቀመንበሩ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና ህወሓት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዱትን እርምጃ አድንቀው በፖለቲካዊ ውይይታቸው እንዲቀጥሉም አበረታተዋል፡፡

በተጨማሪም ሊቀመንበሩ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዘላቂ ሰላምና መግባባት እንዲፈጠር ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ በድርድር ለመፍትሄ ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት አመስግነዋል።
ሊቀመንበሩ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና በአፍሪቃ ህብረት መሪነት የተጀመረውን የሰላም ሂደት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በያይኔአበባ ሻምበል

ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *