ቤንዚል አርከፍክፎ እሳት በመለኮስ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ተከሳሽ 14 ዓመት እስራት ተወሰነበት፡፡

ከአስራ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ቤንዚል አርከፍክፎ እሳት በመለኮስ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ተከሳሽ በፅኑ እስራት ተቀጣ፡፡

በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት የተነሳውን ሁከት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የኤስ ደብሊው ኤስ (SWS) ንብረት የሆነውን ከአስራ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ቤንዚል አርከፍክፎ እሳት በመለኮስ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ በፅኑ እስራት ተቀጣ፡፡

ቡታ በትሩ አደሬ የተባለው ተከሳሽ የከባድ ውንብድና እና የእሳት ቃጠሎ ማድረስ ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 671/1/ሀ/ እና 494/2/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፉ በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል፡፡

ተከሳሽ ከሌሎች ካልተያዙ ግብረ-አባሪዎቹ ጋር በመሆን ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ በግምት ከ5፡00 እስከ 11፡00 ሰዓት ባለው ግዜ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው በሉ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ንብረትነቱ የኤስ ደብሊይው ኤስ የሆኑ ንብረቶችን በወቅቱ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት የተፈጠረውን ግርግር እንደ ምክንያት በመጠቀም ዱላ እና ድንጋይ በመያዝ ከአባሪዎቹ ጋር በመሆን የድርጀቱ አጥር ውስጥ ዘለው በመግባትና የድርጅቱን ጥበቃዎች ደብድበው በማባረር ካሜራዎችን፣ የበር እና የመስኮት መስታዎቶችን በመሰባበር ወደ ውስጥ ገብተው 4 ኮምፒተር፣ ቦርሳ፣, አስር የቪ-8 መኪና ጎማ፣ 15 የከባድ መኪና ጎማዎች፣ 2 የደህንነት ካሜራዎች፣ 2 ፕሪተር ማሽን፣ 14 ስማርት ሞባይሎች፣ 5 የመኪና ባትሪ፣ 12 ኦክስጂን ሲሊንደር፣ 7 የአየር ማቀዝቀዣ፣ በአጠቃላይ 1,403,000 /አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሶስት ሺህ/ ብር የሚገመት ንብረት፤ እንዲሁም በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ 8 ኒሳን ፒካፕ መኪና፣ አንድ የእቃ ማጓጓዣ ፎር ክሊፍት፣ 350 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ተገጣጣሚ የቢሮ እና የመኖሪያ ቤት፣ 9 ጀኔሬተሮች፣ 6 ፍሪጆች፣ አንድ የደህንነት ካሜራ፣ 20 ኮንፎርቶች፣ 15 ተደራራቢ የብረት አልጋዎች እንዲሁም የቢሮ ወንበር እና ጠረጳዛ በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 16,510.692.00 /አስራ ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ አስር ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ሁለት/ ብር የሚገመቱ ንብረቶች ቤንዚል አርከፍክፎ እሳት በመለኮስ ከፍተኛ ጉዳት ወይም አደጋ ያስከተለ በመሆኑ በፈፀማቸው ሁለት የከባድ ውንብድና እና እሳት ቃጠሎ ወንጀል ተከሷል፡፡

ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ “እኔ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች፣ የኤግዚቢት እና የሰነድ ማስረጃዎች በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ማስተባበል ባለመቻሉ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።

በዚህም መሰረት ተከሳሽ ከዚህ በፊት የጥፋተኝነት ሪከርድ የሌለበት߹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ እና ሌሎች ሁለት ማቅለያዎች በድምሩ 4 የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውለት በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

ምንጭ፡- ፍትህ ሚንስቴር

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *