በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ የደን ቃጠሎዎች 90 ከመቶ የሚሆኑት በሰዉ ሰራሽ ምክንያት የሚከሰቱ ናቸዉ ተባለ፡፡

ሃገራችን በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠማት የደን ቃጠሎ ምክንያት የሰለጠኑ ባለሙያዎች እና በቂ የእሳት ማጥፊያ ትጥቆች ባለመኖራቸው ሳቢያ ደኖቻችን ሲወድሙ በአይናችን ለማየት ተገደናል፡፡
በተደጋጋሚም ከጎረቤት ኬንያ እስከ እስራኤል ባለሙያዎች እና መሳሪያዎችን አስመጥተን ደኖቻችንን ለመታደግ ጥረት አድርገናል፡፡

በደን አካባቢ የሚነሱ ቃጠሎዎችን ለመከላከል ዋነኛ ከሚባሉት ትጥቆች መካከል አንዱ የእሳት ማጥፊያ አውሮፕላን ነው፡፡
ለመሆኑ እንደ ሃሳብ ቀርቦ የነበረው የእሳት ማጥፊያ አውሮፕላን ግዢ ምን ላይ ደረሰ ስንል በኢትዮጲያ ደን ልማት የደን አደጋ መከላከል ዝግጁነት ዳይሬክተር አቶ አዱኛ አበበ ጠይቀናል፡፡

አቶ አዱኛም እርዳታ ሰጪ ተቋማትን ጠይቀን የነበረ ቢሆንም ፋቃደኛ አልሆኑም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ምክንያታቸው በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው የደን ቃጠሎ እና ሰደድ እሳት አንፃር እኛ ሃገር የሚከሰተው ቃጠሎ ቀላል ይሆንባቸዋል ነዉ ያሉት፡፡

በራስ አቅም የእሳት ማጥፊያ አውሮፕላን ለመግዛት በተለያዩ መድረኮች ላይ በማንሳት እና በመወትወት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሊሳካ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

የደን ቃጠሎ ዋነኛ ተብለው የተለዩ አካባቢዎችን የዘረዘሩት አቶ አዱኛ በምእራብ አካባቢ አሶሳ፣ እንዲሁም ባሌ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰሜን ተራሮች አካባቢም ቃጠሎዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ለቃጠሎዎቹ ዋነኛ ምክንያት ሰው ሰራሽ ነው ያሉት ዳይረዴክተሩ፣ በተፈጥሮ የሚነሱ የደን ቃጠሎዎች ከ10 ከመቶ አይዘሉም ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከደን ቃጠሎ ጋር በተያያዘም በሃገር ውስጥ ከድርቅ እና ጎርፍ ባሻገር የአደጋ ስጋት ስራዎቻችንም ሰፊ ክፍተት የሚታይባቸው መሆናቸውንም አቶ አዱኛ ነግረውናል፡፡

አቶ አዱኛ ህብረተሰቡ ለደን እና አካባቢው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአብዱሰላም አንሳር

ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *