የሩስያው ፕሬዝደንት የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሃገር ውጭ ታይተዋል፡፡

ቭላድሚየር ፑቲን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቱርክሜኒስታን ገብተዋል፡፡
ይህም ከአራት ወራት በላይ ከቆየው እና ከቀጠለው የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ወዲህ የተካሄደ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ነው፡፡
በቀጣይ ፑቲን ከታጃኪስታኑ ፕሬዝደንት ኢሞ-ማሊ ራህሞን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተለይም የድርድር ጉዳዮችም በቀዳሚነት ከሚነሱት መካከል መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ወር መገናኘታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ የታጃኪስታኑ ፕሬዝደንት የሩስያን የድል በአል የታደሙ ብቸኛው የሃገር መሪ እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡
የአውሮፓ ህብረት ወደቀደመው የከሰል ዘመን እየተመለሰ ይገኛል ተብሏል፡፡

በርካታ የህብረቱ አገራት ለአደጋ ጊዜ ብለው በዝግ ያቆዩዋቸውን የሃይል አማራጭ ኢንደስትሪዎች ዳግም እየከፈቱ እንደሚገኙም ተዘግቧል፡፡ ከእነዚህ ሃገራት መካከል ጀርመን፣ ኦስትሪያ እና ኔዘርላንድ በቀዳሚነት የተጠቀሱ ሲሆን በከሰል የሚሰሩ ማእከሎቻቸውን ዳግም ወደስራ መመለሳቸው ተመላክቷል፡፡

ጀርመን ከዚህ ቀደም ሩስያ የአውሮፓ ህብረት ላይ የንግድ አሻጥር ሰርታለች ስትል መወንጀሏ ተሰምቷል፡፡ በህብረቱ በኩል ሩስያ በድንገት የነዳጅ አቅርቦት ታቋርጣለች የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳንዣበበም ሲነገር ቆይቷል፡፡
በጀርመን በኩል ውሳኔው መራራ ቢሆንም ኢንደስትሪዎቹ ወደስራ እንዲገቡ ከውሳኔ መደረሱ ከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣን መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
እንደ ባለስልጣኑ ከሆነ ይህን ባናደርግ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ እንወድቃለን ብለዋል፡፡
የቡድን 7 አባል ሃገራት በሩስያ የመከላከያ ኢንደስትሪዎች ላይ ማእቀብ መጣሉን አሜሪካ አስታወቀች፡፡
ይህ ማእቀብ የመከላከያ መስሪያ ቤቱ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር ይሆናል ተብሏል፡፡
በሩስያ መከላከያ መስሪያ ቤት ላይ የተጣለው ማእቀብ፣ ሃገራቱ ከውይይታቸው በኋላ ያሳለፉት ውሳኔ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ማእቀቡ የሩስያ መከላከያ ኢንስትሪዎች በምንም መልኩ የምእራባዊያንን የጦር መሳሪያዎች መገልገል እንዳይችል የሚያደርጉ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

በአብዱሰላም አንሳር

ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *