የውጭ ማስታወቂያ ደንብ መፅደቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

ደንቡ በከተማው የሚተከሉ፣ የሚለጠፉ ወይም በማናቸውም መንገድ የሚሰራጩ የውጭ ማስታወቂያዎች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲሰራጩ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡
ይህም አደረጃጀትና አሰራርን በማዘመን ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ጤናማ የውጭ ማስታወቂያ እንዲኖር እንዲሁም ኢንዱስትሪው ሰፊ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የሥራ እድል እንዲፈጥር ለማድረግ ያግዛል ነዉ የተባለዉ።

ይህ ደንብ በቢል ቦርድ፣ በማስታወቂያ ሰሌዳ፣ በኤሌክትሮኒክ ስክሪን ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል የሚሰራጭ፣ እንዲሁም በሕንጻ፣ በግድግዳ፣ በጣራ፣ በማናቸውም ስትራክቸር ወይም በትራንስፖርት ተሽከርካሪ፣ በተንሳፋፊ ፊኛ ወይም መሰል ነገር ላይ የሚሳል፣ የሚፃፍ፣ የሚለጠፍ፣ የሚተከል ማስታወቂያን ይመለከታል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል በተንጠልጣይ ነገር፣ በፖስተር፣ በስቲከር፣ በተባዛ በራሪ ወረቀት፣ በብሮሸር፣ ሊፍሌት፣ ፍላየር የሚሰራጭ፣ በድምጽ ካሴት፣ በድምፅ ማጉያ መሳሪያ የሚሰራጭንም ያጠቃልላል።

ሆኖም የመንገድ አቅጣጫ ጠቋሚ፣ የትራፊክና የአውቶቡስ ፌርማታ ምልክትን፣ የመንገድ ስምን ወይም ቁጥርንና መሰል የሕዝብ አገልግሎት መረጃ ሰጪ ምልክቶችን አይጨምርም ተብሏል።

ማንኛውም በምስል፣ በቅርጽና በድምፅ፣ በምስል የሚተላለፉ የውጭ ማስታወቂያዎች የፌደራል መንግስትና የከተማ አስተዳደሩን ህጎች፣ የህዝቡን ባህል፣ እምነት፣ ቋንቋና እሴቶች የማክበር ግዴታ አለባቸው መባሉን ኢትዮ ኤፍኤም ከባለስልጣኑ ሰምቷል።
እንዲሁም ማንኛውም የውጭ ማስታወቂያ ከመሰራጨቱ በፊት በባለሥልጣኑ እና በሚመለከተው አካል የሚያወጣውን የብቃትና የጥራት ደረጃ መመሪያ የሚያሟላ የውጭ ማስታወቂያ መሆን አለበት ነው የተባለው።
በማንኛውም ሁኔታ የውጭ ማስታወቂያ ማሰራጨት የሚቻለው በአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ፈቃድ ብቻ መሆኑንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ያደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.