የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት 18 ከሚሆኑ ባንኮች ጋር ሰነዶችን በonline ለማረጋገጥ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን አሰታውቋል፡፡

ተቋሙ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በማዘመን ላይ እንደሚገኝ የአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ አብነት ሰለሞን ለኢቲዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙ ከሁሉም የሐገሪቱ ባንኮች ጋር እያደረገ ያለው የቀጥታ የመረጃ ልውውጥ ስምምነትና ትግበራ የተገልጋዩን ገንዘብ ፣ ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ እና የዜጎችን ሃብትና ንብረት ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፆ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

ከነበሩት ባንኮች በተጨማሪ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ከአማራ ባንክ እና ስንቄ ባንክ ጋር ሰነዶችን በቀጥታ (online) ለማረጋገጥ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መፈራረሙን ነው አቶ አብነት የተናገሩት።
አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ዘምዘም ባንክን ጨምሮ ከ 16 መንግስታዊና የግል ባንኮች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ መፈራረሙ የሚታወስ ነው::

የመግባቢያ ስምምነቱ በተለይም የዉክልና ሰነዶችን ትክክለኛነትና ህጋዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የማጭበርበር ወንጀሎችን ለማስቀረትና በዉክልና የሚንቀሳቀሱ የባንክ ሂሳቦችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የሰነዶችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ቀደም ሲል የነበረውን ለእንግልት የሚዳርግ አሰራርን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ተብሏል፡፡

በረድኤት ገበየሁ

ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *