የኢትዮ -ሱዳን ድንበር የጸጥታ ሁኔታ በአካባቢዉ ነዋሪዎች አንደበት ሲገለጽ! ስለቀጣይ መፍትሄዉስ ምሁራን ምን ይላሉ?

የሱዳን ጦር በከባድ ጦር መሳሪያ የታገዘ ድብደባ እያደረገ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እንደገጠማቸዉ የአብዱራፊ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት መንግስት ከለላ እንዲያደርግላቸዉም ጠይቀዋል፡፡
የአካባቢዉ አርሶ አደሮች ለአመታት ያርሱት የነበረዉን መሬታቸዉን በሱዳን ወታደሮች ከተነጠቁ ሁለት አመት እንደሆናቸዉና በዚህም ከባድ የኢኮኖሚ ጫና እንዳሳደረባቸዉም ነግረዉናል፡፡

አሁን ደግሞ ከኢኮኖሚ ጫናዉም አልፎ ወደ ህልዉና ጥያቄ ተሸጋግራል ነዉ የሚሉት፡፡
ምክንያቱም በእነ ጀነራል አልቡርሃን የሚመራዉ የጦር ክንፍ በምእራብ አርማጭሆ አብዱራፊ ተብላ በምትጠራዉ ከተማ ጭምር ከባድ መሳሪያዎች መተኮስ በመጀመሩ ለክፍተኛ ስጋት መዳረጋቸዉን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
እናም መንግስት የሱዳንን ትንኮሳ ደርሶ ያስታግስልን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ላይ ባሰፈሩት መልእክት ኢትዮጵያና ሱዳን ያጋጠሟቸውን ችግሮች በወንድማማችነትና በመልካም ጉርብትና መንፈስ የመፍታት አቅም አላቸው ሲል ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ችግር መኖሩ ግልፅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ነገር ግን ሁለቱ ሀገራት እነዚያን ችግሮች ለመፍታት ሊጥሩ እና ሊተባበሩ ነው የሚገባው ብለዋል።

ባጎረስኩ ተነከስኩ እንዲሉ የራሷን የቤት ሥራ ትታ የጎረቤት ሀገር ሱዳንን አለመረጋጋት ለመፍታት ብዙ ዋጋ የከፈለችዉ ኢትዮጵያ በምትኩ ከካርቱም የተሰጣት ስጦታ ምስጋና ሳይሆን ዘረፋ ነዉ፡፡
ጎረቤት አገር ሱዳን የኢትዮጵያን ዉስጣዊ ችግር እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅማ በጋላቢዎቿ እየተመራች በማን አለብኝነት የኢትዮጵያን ግዛት ከተቆጣጠረች እነሆ ሁለት አመታት እየተቆጠሩ ነዉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳንን እርምጃ በሃይል ሳይሆን በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ለመመለስ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም የአልቡርሃን አስተዳደር ግን ይባስ ብሎ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ የሆነ ጦረነት ለማወጅ እየተንደረደሩ ይመስላሉ፡፡

በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የዓባይ ዉሓ ተመራማሪና የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ አበበ ይርጋ የሱዳን እርምጃ ከኢትዮጵያ ዉስጣዊ ችግር የመነጨ ነዉ ይላሉ፡፡
ለዚህ ደግሞ አቶ አበበ እንደማሳያ የሚያነሱት ኢትዮጵያ ዉስጣዊ ችግር በገጠማት ቁጥር የሱዳን ሃይሎች የተለያዩ ትንኮሳዎችን በታሪክ አጋጣሚ ማድረጋቸዉን ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ ዉስጣዊ አለመረጋጋት ለሱዳን ፖለቲከኞች ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል የሚሉት አቶ አበበ ከዚያ ባለፈ ግን የአሁኑ ትንኮሳ የሶስተኛዉን ዙር የግድቡን ዉሃ ሙሌት ለማስተጓጎል እንደሆነም ያነሳሉ፡፡

የጂግጂጋ ዩንቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ ሰለሞን ጓዴ በበኩላቸዉ ፤ የሱዳን የጦር አመራሮች ሀገር ዉስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ችግር ስላለባቸዉ ያንን ለማስተንፍስና አጀንዳ ለማስቀየር ነዉ ትንኮሳዎችን የሚደርጉት ባይ ናቸዉ፡፡

ከዚያ ባለፈ ግን አካባቢዉ ከፍተኛ የሆነ ስትራቴጂክ ቦታ በመሆኑ ያንን ላለማጣት እንዶሆነና ለዚህ ደግሞ ከሱዳኖች በተጨማሪም የሌሎች ሀገራት ዕጅ እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

ቋሚ ጥቅም እንጅ ቋሚ ጠላትና ወዳጅ የለም የሚለዉ አስተሳሰብ እንዳለ ሆኖ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸዉ አገራት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

በጉዳዩ ላይ ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረገዉ ሱዳዊዉ ጋዜጠኛ አሊ ያህያ ሲናገር፤ ያሁኑ ጠብ አጫሪነት የሱዳን ህዝብ ፍላጎት እንዳልሆነና የሱዳን ጦር በሁለት ገፊ ምክንያቶች ነዉ ይህንን ትንኮሳ የሚያደርገዉ ባይ ነዉ፡፡

“አንድም የህዳሴ ግድቡን የዉሃ ሙሌት ለማስተጓጎል ሁለተኛ ደግሞ ሀገር ዉስጥ የተደገሰለትን ተቃዉሞ ለማዘናጋት” ነዉ ይላል፡፡

ከእነ ጀነራል አልቡርሃን ጀርባ የተወሰኑ የሱዳን ፖለቲከኞች ስለመኖራቸዉ የሚገልጸዉ ሱዳናዊዉ ጋዜጠኛ፤ ነገር ግን እንዲህ አይነቱን ድርጊት የምታስፈጽመዉ ግብጽ መሆኗ ሊታወቅ ይገባል ሲልም ሃሳቡን ያክላል፡፡

እናም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ይህንን ተገንዘበዉ ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ሲል ተማጽኗል፡፡

ኢትዮጵያ ከጦርነት ሰላም ይበጀናል በሚል ላለፉት ሁለት አመታት ዲፕሎማሲን አማራጭ አድርጋ ቆይታለች፡፡
አሁንም ቢሆን ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን በመግለፅ ላይ ትገኛለች፡፡
ለመሆኑ የኢትጵያ ቀጣይ ዉሳኔ ምን ቢሆን ነዉ አትራፊ የሚያደርጋት በሚለዉ ላይ አቶ አበበ ይርጋ ሲመልሱ “ዲፕሎማሲን መጠቀም” መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ጓዴ ግን “ትዕግስትም ልክ አለዉ” ባይ ናቸዉ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ከሰሞኑ በሰጠዉ መግለጫ ሱዳን ከድርጊቷ ካልተቆጠበች አስመማማኝ ሃይል በቦታዉ እንዳለ መግለጹ የሚታወስ ነዉ፡፡
የአፍሪካ ህብረትም ሁለቱም ሃገራት ከጦርነት ጉሰማ እንዲታቀቡ በመጠየቅ ላይ ይገኛል፡፡

በአባቱ መረቀ
ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *