የአለም ጤና ድርጅት የአደጋ ጊዜ ምላሽ ረዳት ጄኔራል ኢብራሂማ ሶስ ፎል እንዳሉት በጤና አጠባበቅና ተደራሽነት ላይ አንዳንድ ቀጠናዎች ላይ የጤና አደጋዎች እየጨመሩ ነው ብለዋል።
ምንጊዜም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ሰዎች እንዳይራቡ መከላከል ቢሆንም በሽታን ለመከላከልና ህይወትን ለማዳን በተመሳሳይ ጊዜ የጤና ምላሻችንን ማጠናከር አለብን ሲሉ ፎል በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
የአለም ጤና ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር ናይሮቢ ውስጥ በድንገተኛ የጤና አደጋ ተጎድተዋል የተባሉትን ሰባት ሀገራት ማለትም ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳ እና ከሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ጋር ለመቀናጀት የሁለት ቀን ስብሰባ ጠርቶ የነበረው።
በስብሰባው የተባበሩት መንግስታት እና የተለያዩ አጋሮችም በናይሮቢ ውስጥ ምላሹን የሚያስተባብር እና ወደ የሚፈልጉበት ቦታ ሕይወት አድን የሆኑ የህክምና አቅርቦቶችን ለማድረስ የሚያስችል ማዕከል እያዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
እነዚህ አቅርቦቶች የተለያዩ መድሀኒቶች ፣ ክትባቶች እንዲሁም የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ህጻናት ለማከም የሚያስፈልጉ መድሀኒቶች እና መሳሪያዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አስከፊ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋረጠበት ምክንያትን ሲያብራራ፣ በ40 አመታት ውስጥ የከፋ የተባለለት ሲሆን ምክንያቶቹም በግጭት ሳቢያ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ፣ የአለም የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ መናር እና ወረርሽኞች ያስከተለሉት ተፅዕኖ ነው ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበሽታው በተጠቁ አገሮች ውስጥ ካሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሮች ጋር በመሆን የበሽታ መከላከያ ዘዴዎችን በመዘርጋት የበሽታዎችን ወረርሽኝ በፍጥነት ለመለየት እና ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ማስታወቁን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡
በረድኤት ገበየሁ
ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም











