የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ በአማራ ተወላጆች ላይ በደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ላይ ሁለቱም ምክር ቤቶች ተባባሪ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።
ፖርቲው በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ፣ በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ የተቀናጀ ፣ተከታታይና ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፀም፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክርቤት ጥቃቱን በግልፅ አለማውገዛቸው የጥቃቱ ተባባሪ ናቸው ብዬ እንዳምን አድርጎኛል ብሏል፡፡
ሁለቱ ምክር ቤቶች በክልሉ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት በግልፅ አለማውገዛቸው በአማራ ህዝብ ላይ ያላቸውን ንቀት በግልፅ ያሳያል ብሏል ፖርቲው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር በለጠ ሞላ በመግለጫው ላይ እንዳሉት፣ በአማራ ንፁሃን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መንግስት ካላስቆመ ሀገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ልትገባ እንደምትችል አሳስበዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን በክልሉ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ወለጋና አካባቢው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንዲሆን ሲል የመፍትሔ ሀሳቡን አቅርቧል።
በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ሀዘን እንዲታወጅ የጠየቀው አብን፣ ከዚህ ባለፈ ግጭቱ ያቀጣጠሉት የኦነግ፣የኦፌኮና የክልሉ አመራሮች በህግ እንዲጠየቁ ሲልም አሳስቧል።
በአባቱ መረቀ
ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም











