በሀገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የሆቴል ግብአት አቅራቢዎች ከሆቴሎችጋር የሚገናኙበት ኤክስፖ በኤሊያና ሆቴል አዘጋጅነት ነዉ በመካሄድ ላይ የሚገኘዉ፡፡
አሁን በሀገራችን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ላይ ተዳምሮ በርካታ ነገሮች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡበት በዚህ ሁኔታ፣ ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ጋር በጋራ የሚሰራበት ሂደት መፈጠሩ የተሻለ ዉጤት ያመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሰው ገልጸዋል።
ለሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉ የሚያገለግሉ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ጭምር ለዘርፉ ድጋፍ ሲደረግ እንደነበርም ተናግረዋል።

በኮቪድ 19 ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ መነቃቃት እንዲኖር እና የተቀዛቀዘውን የሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም ሃላፊዋ ገልጸዋል።
የሆቴል ማሰልጠኛ ተቋማት፣ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ድርጅቶች፣አየር መንገድ፣ ትራንስፖርት ፣የምግብ እና መጠጥ፣ የንፅህና መጠበቂያ አቅራቢዎች፣ደህንነት እና ጥበቃ፣የህክምና፣የመዝናኛ እንዲሁም የስዕል አቅራቢዎች የሚሳተፉበት ነው ተብሏል።
ዛሬ እና ነገ በሚካሄደው በዚህ ኤክስፖ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች እና ከ10 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በእስከዳር ግርማ
ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም











