የመሬት አስተዳደር የንብረት ግምት ባለሙያ የሆነች አንዲት ግለሰብ 10 ሺ ብር ጉቦ ስትቀበል እጅ ከፍንጅ መያዟን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
የጉለሌ ክ/ከተማ የመሬት አስተዳደር የንብረት ግምት ባለሙያ የሆነችው ግለሰብ አንድን ባለ ጉዳይ ጉዳይህን እኔ እጨርስልሀለሁ በማለት 10ሺ ብር ጉቦ ስትቀበል ሀምሌ 6 ቀን 2014 ዓ/ም እጅ ከፍንጅ ተይዛ አስፈላጊው ምርመራ ተጣርቶ ክስ እንደተመሰረተባት የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የግል ተበዳይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከድንበር ጋር የተያያዘ ጉዳዩን ለማስጨረስ በሄደበት አጋጣሚ ግለሰቧ 30 ሺህ ብር ጉቦ የጠየቀችው ሲሆን 10ሺ ብር ቅድሚያ እንደሰጣት እና ቀሪውን 20 ሺህ ብር ደግሞ ጉዳዩ ሲያልቅ ለመወሰድ መጠየቋን የግል ተበዳይ ለክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ አሳዉቋል፡፡
በመሆኑም ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ/ም ጉቦውን ስትቀበል በፖሊስ እጅ ከፍንጅ ተይዛ አስፈላጊው ምርመራ ተጣርቶ ክስ እንደተመሰረተባት የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
ማህበረሰቡ መሰል ወንጀል ፈፃሚዎችን ለህግ አካል አጋልጦ የመስጠት ልምዱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ተናግሯል፡፤
ወደፊትም ህዝብን እና መንግስትን የሰጣቸውን እምነት በማጉደል በማህበረሰቡ ላይ በደል የሚፈጽሙ አካላትን ወደ ህግ ለማቅረብ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም











