ናይጂሪያ ሞተር ብስክሌትን ለደህንነት ስትል ልታግድ ነው፡፡

ናይጂሪያ ይህንን አይነት ውሳኔ ለመወሰን የተገደደችው በሞተር ብስክሌት እየተጓዙ ጥቃት የሚፈጽሙ እስላማዊ ታጣቂዎች በመበራከታቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡
ይህ ወሳኔ የተሰማው ከቀናት በፊት በሞተር ብስክሌት የሚጓዙ ታጣቂዎች በሰሜን ምዕራብ የናይጄሪያ ግዛት ካትሲና ውስጥ፣ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች አምስት ፖሊሶችን ጨምሮ 17 ንጹሀን ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው፡፡

በዚሁ በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት 300 የሚሆኑ በሞተር ብስክሌት የመጡ ታጣቂዎች ካንካራ በሚባል ቦታ ላይ የሚገኝን ፖሊስ ጣቢያ ኢላማ አድርገው ጥቃት ፈጽመዋል።
እንደ ቢቢሲ አፍሪቃ ዘገባ ከሆነ እነዚሁ ታጣቂዎች በፖሊስ ጣቢያው አቅራቢያ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ በመግባት ሦስት ሰዎችን ገድለዋል፤ከብቶችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶችንም ዘርፈዋል።

በተመሳሳይ ሌላ ጥቃት ደግሞ ታጣቂዎች ፋሳካሪ በሚባለው አካባቢ በሚገኙ በርካታ መንደሮች ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎችን ገድለዋል፡፡

ካትሲና ግዛት በናይጄሪያ በታጣቂዎች ከፍተኛ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው ቦታዎች አንዷ ስትሆን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ ትውልድ ስፍራ ናት።

በያይኔአበባ ሻምበል
ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *