በኦሮሚያና ሶማሊያ ክልሎች በድርቅ የተጎዱ ሰዎች ትኩረት ሊሰጣቸዉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሁለቱ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ እና ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ ከየካቲት 14 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በድርቁ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብለው በተለያዩ አካላት በይፋ እውቅና የተሰጣቸው አካባቢዎች በመዘዋወር ያዘጋጀውን ባለ 50 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት ክትትል የተደረገባቸው ቦታዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎች ቢሆኑም በዚህ ሪፖርት የተሸፈነው ወቅት የተከሰተው ድርቅ ከዚህ በፊት ከነበሩት አደጋዎች በተለየ መልኩ የተራዘመ ማለትም ከ 2 እስከ 4 የዝናብ ወቅቶች ያልዘነበበት እንዲሁም ሰፊ ቦታዎችን ያካለለ እንደሆነ የክትትሉ ግኝት ያሳያል፡፡ በመሆኑም ማኅበረሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ ተሻሉ ቦታዎች ተዘዋውሮ ከድርቁ ተጽዕኖ ለማምለጥ አልቻለም ብሏል፡፡

በድርቁ ጉዳት ሳቢያ በተለይ በቂ ውኃና ምግብ ባለመኖሩ ሰዎች ለተለያዩ የጤና እክሎች ተዳርገዋል፡፡

በምግብ እጥረት ምክንያት ሰውነታቸው የከሳ፣ ሆዳቸውና እግራቸው ያበጠ በዚህም ታመው የተኙ ሰዎች አሉ ነዉ ያለዉ ኢሰመኮ፡፡

የጤና ግልጋሎት መስጫ ተቋማት በአካልም በኢኮኖሚም ተደራሽ አለመሆናቸውንም ክትትሉ አሳይቷል፡፡ የጤና ግልጋሎቶችን ለራሳቸው ማግኘት ለማይችሉ የድርቁ ተጎጂዎች የጤና ግልጋሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች ውስን መሆናቸዉንም አንስቷል፡፡

በዚህ ምክንያት ተጋላጭ የሕብረተሰቡ ክፍሎች በተለይም አረጋውያን እና ሕፃናት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል።

በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በተፈናቃይ ካምፖች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተግባራት አለመከናወኑ እና የተፈናቃዮችን ጤና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል እንደ ወረርሽኝ የመሰለ በሽታ ተጋላጭነት ነበር፡፡ ይህም የድርቅ ተጎጂዎችን የጤና መብት ከማረጋገጥ አንጻር ክፍተት እንዳለ ያመላክታል ብሏል፡፡

በሁለቱም ክልሎች የቅድመ ጥንቃቄ እና የማሳወቅ ስራዎች አለመሰራታቸዉ የሚሰጠዉ መፍትሄ የዘገየ እንዲሆን አድርጎታል ብሏል

ኮሚሽኑ መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በድርቁ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ድጋፍ ፈላጊዎች ባሉበት ቦታ እርዳታ እንዲያገኙ እንዲያደርግ፣ እርዳታ የሚገኝበትን ቦታ እና ሁኔታ እንዲያሳውቅ እና ያለ በቂ መረጃ ለሚፈናቀሉ ሰዎች አፋጣኝ እርዳታ ለማድረግ የሚያስችል የመጠባበቂያ እርዳታ ዝግጁ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.