የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ የነበረችውን ወጣት የገደሉ ሦስት ወንጀለኞች የ13 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደባቸዉ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳለዉ ግለሰቦቹ ከልዩ ልዩ ማህበራዊ መብቶቻቸው ለአምስት አመት እንዲሻሩም ተወስኖባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ የነበረችው ወ/ሮ እፀገነት አንተነህ መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ/ም በግምት 12 ሰዓት ተኩል ገደማ ወደ ስራ ለመሄድ ከሰፈሯ ተነስታ የመስሪያ ቤቷን ሰርቪስ እስከምታገኝበት ቦታ ለመጓዝ ትራንስፖርት በመጠበቅ ላይ እንዳለች በረከት ብርሃኑ ፣ ዮናስ ካሳ እና ዳግም ውብሸት የተባሉ ሦስት ግለሰቦች በሰሌዳ ቁጥር ኮድ1-34039 ኦ/ሮ ባጃጅ ካሳፈሯት እና አስገድደው ወደ ሰዋራ ስፍራ በመውሰድ ገንዘብና ልዩ ልዩ ንብረቷን ይሰርቃሉ፡፡

ከዛም በኋላ በመግደል አስከሬኗን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዮ ቦታው ሰላም ፍሬ ጤና ጣቢያ አካባቢ መንገድ ላይ ጥለው መሰወራቸውን የተከሳሾቹ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

በወቅቱ ወንጀሉን የፈፀሙትን ግለሰቦች ለማወቅ አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ባደረገው ክትትል ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወንጀሉን በፈፀሙ በዘጠነኛው ቀን መስከረም 15 ቀን 2012 ዓ/ም በቁጥጥር በማዋል በማግስቱ የወንጀሉን አፈፃፀም መርተው እንዲያሳዩ መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

የተከሳሾቹን ጉዳይ ሲመለከተት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ/ም በዋለው ችሎት በረከት ብርሃኑ ፣ ዮናስ ካሳ እና ዳግም ውብሸት እያንዳንዳቸው በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማስተላለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በወንጀል ህግ አንቀፅ 123 መሰረት ከህዝባዊ መብቶቻቸው በተለይ በምርጫ ላይ ተካፋይ ከመሆን ፣ ለህዝብ አገልግሎት ስራ ከመመረጥ ፣ በሰነድ ወይም የውል ስምምነት ላይ ምስክር ከመሆን ፣ በቤተ ዘመድ ካለው መብት በተለይም የወላጅነት ስልጣን ከመያዝ ችሎታ ፣ ከሞግዚትነት እና የንግድ ፈቃድ የሚያስፈልገውን የሙያ ፣ የኢንዱስትሪ ወይም የንግድ ስራ ከመስራት መብታቸው ለአምስት ዓመት እንዲሻሩ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.