1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል፡፡

በሀገራችን በዚህ አመት ብቻ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር ድኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ካለፈው አመት ከነበረው ቁጥር 10 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች በወባ መያዛቸውን ገልጸዋል።
በሀገራችን 75 በመቶ የሚሆነው መልክዓ ምድር ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ደረጄ፣ በእነዚህ ቦታዎችም 52 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቻችንም ይኖራሉ ነዉ ያሉት፡፡

በእነዚህ ቦታዎች በአመት ሁለት ጊዜ ወባ እንደሚከሰት የገለፁት ሚኒስቴር ዲኤታው፣ በተለይ የዝናብ ወቅቶችን ተገን አድርጎ በጣም ብዙ ሰዎችን እንደሚጎዳም አንስተዋል።

በተለይም በኮንስትራክሽን ፣መስኖ እና ግብርና ስራዎች በሚበዙበት ቦታዎች ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ቦታዎች ናቸው ያሉት ዶክተር ደረጄ፣ ድርቅ የነበረባቸው ቦታዎች ፣መጠለያ ካምፖች እና የፀጥታ ችግር ያለባቸው ቦታዎችም ምቹ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በማህበረሰቡ ደረጃ ያለው አረዳድ እና የግንዛቤ ማነስ እንዲሁም ወባን እንደ ገዳይ በሽታ አለመመልከት ፣አጎበርን በአግባቡ አለመጠቀም ለበሽታው መስፋፋት ትልቅ ድርሻ አለው ነዉ ያሉት፡፡

በዚህም አማራ፣ደቡብ ፣ደቡብ ምዕራብ ፣ኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልሎች በከፍተኛ ደረጃ በሽታው የተከሰተባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል ።
5 ነጥብ 5 ሚሊየን መመርመሪያ ኪት ለሁሉም ጤና ተቋማት መሰጠቱን፣4.5 ሚሊዮን ፀረ ወባ መድሐኒት እና 3 ሚሊዮን የአልጋ አጎበር መከፋፈሉን እንዲሁም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቤቶች የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ገልፀዋል።

በእስከዳር ግርማ
ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *