ከህወሃት ጋር ለመደራደር በየትኛዉም ጊዜና ቦታ ዝግጁ ነኝ—-ፌደራል መንግስት!

መንግስት ከህወሃት ጋር በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሓት ጋር በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለመደራደር መዘጋጀቱን የድርድር ቡድኑ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ናቸዉ ያስታወቁት፡፡
የድርድር ቡድኑ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሌላኛው የድርድር ቡድኑ አባልና ከፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር በመሆን ከተለያዩ አካላት ጋር ንግግር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከተባበሩት መንግስታት፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን እና ብሪታኒያ አምባሳደሮች ጋር አምባሳደር ሬድዋንና ዶ/ር ጌዲዮን ቲሞቲዮስ፤ መወያየታቸው ታዉቋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ እንደገለጹት፤
የፌዴራል መንግስቱ ለሰላም አማራጭ ያለውን ዝግጁነት አብራርተዋል።

መንግስት በየትኛውም ጊዜ፣ ቦታና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የሰላም ንግግሩ መመራት ያለበት በአፍሪካ ህብረት እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፤ ህብረቱ ከፈለገው አካል የሎጅስቲክ ድጋፍ መጠየቅ እንደሚችል አመልክተዋል።

ከተባባሩት መንግስታት የባለሙያዎች ኮሚሽን ልዑክ ጋር በትብብር ለመስራትና ምቹ ከባቢን ለመፍጠር የተደረገውን ንግግር በተመለከተም ገለጻ መደረጉን ጠቅሰው፤ ቡድኑ ወደ መቀሌ መጓዝ እንደሚችል እንደፈቀደለት አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ሕወሃት ከፌደራል መንግሥት ጋር ለሚያደርገው ድርድር ቅድመ ሁኔታና የጊዜ ገደብ ማስቀመጡን የሕወሃት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔል መናገራቸዉ ተዘግቧል፡፡

ዶ/ር ደብረጺዮን ለቪኦኤ እንደተናገሩት ከሰላም ድርድር በፊት መንግሥት ለትግራይ ያቋረጣቸውን መሠረታዊ አገልግሎቶች እንደገና መጀመር እንዳለበት አውስተዋል።

ዶ/ር ደብረጺዮን መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶችን የሚቀጥልበትን ቁርጥ ያለ ቀን አሜሪካኖች ጠይቀው እንዲነግሯቸው የጊዜ ገደብ መስጠታቸውንም ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
መሠረታዊ አገልግሎቶቹ የማይጀመሩ ከሆነ ግን ውጊያ እንከፍታለን ሲሉ ማስጠንቀቃቸዉንም ነዉ ዘገባዉ ያመለከተዉ፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *