ወንጀል የሚፈፅሙበትን ቦታ ቀድመው አይተው እና መርጠው ከጨረሱ በኋላ የትራንሰፖርት ተጠቃሚ መስለው ራይድ ደውለው በመጥራት ያመቻቹት ቦታ ሲደርሱ አሽከርካሪዉን በመግደል መኪናውን እና ስልኩን ይዘው የተሰወሩት ግለሰቦች በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጡ፡፡
እንደ ዐቃቤ ህግ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ የአብስራ ሰለሞን እና 2ኛ ተከሳሽ በላይነው ንጉስ ካልተያዘው ግብረ-አበራቸው ጋር በመሆን ነሃሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት ራይድ ጠርተው አሽከርካሪውን በንፋስ ስልክ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ክልል የሰዎች እንቅስቃሴ ወደማይበዛበት ገባ ያለ ቦታ ጠርተውት ሆራ ትራዲንግ ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ሲደርሱ 2ኛ ተከሳሽ እና ያለተያዘው ግብረ-አበራቸው አሽከርካሪ ንጉስ ከፍያለውን አንገቱን አንቀው በመያዝ ወንበር ስር ሲያስተኙት 1ኛ ተከሳሽም መኪውን እየነዳ ሟችን ወደኋላ በመዞር በተደጋጋሚ በጩቤ ሆዱ ላይ በርካታ ቦታ በመውጋት ህይወቱ ሲያልፍ የሟችን ቪትስ መኪና፣ የሞባይል ስልክ እና ያደረገውን ጫማ አጠቃላይ ድምሩ 758,250 ብር የሚያወጣ ንብረት ወስደው

መሰወራቸውን ተከትሎ ፖሊስ ባደረገው ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲደረግ ቆይቶ በፈፀሙት ከባድ ውንብድና ወንጀል በፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾች ክሱ ፍ/ቤት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት ክደው የተከራከሩ ሲሆን ዐቃቤ ህግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ አስረድተዋል፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ግድያ እና ከባድ ውንብድና ችሎትም የዐቃቤ ህግ እና ተከሳሾችን ክርክር ሲከታተል ከቆየ በኋላ ተከሳሾች በተከከሰሱበት አንቀፅ ስር ጥፋተኛ ናቸው በማለት እያንዳንዳቸው በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡











