የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ስም ሊቀይር መሆኑን ገለጸ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በበሽታዉ ምክንያት እየደረሰ ባለዉ የመገለል ጉዳይ ነዉ ስሙን ለመቀየር ማቀዱን ያስታወቀዉ፡፡

ስሙ ከዘረኝነት ጋር ግንኙነት አለዉ በሚል ብዙ ትችት ከቀረበበት በኋላ፣የዓለም ጤና ድርጅት የበሽታዉን ስም ለመቀየር ዉይይት መጀመሩን ገልጿል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ማህበረሰቡም ለበሽታዉ ስም ይሆናል የሚለዉን እንዲያቀርብ መንገድ እየከፈተ መሆኑን የገለጸ ሲሆን አዲሱ ስም መቼ ይፋ እንደሚደረግ ግን ምንም ያለዉ ነገር የለም፡፡

ድርጅቱ ባወጣዉ መግለጫ ከበሽታዉ ጋር ግንኙነት የነበራቸዉን ሁለት ቫይረሶች ስማቸዉን መቀየሩን ተናግሯል፡፡
ለአብነትም ከዚህ በፊት ‹‹ኮንጎ ቤዚን›› በመባል የሚታወቀዉን ቫይረስ ‹‹ክላድ 1 ወይም 1 ››እና ‹‹ዌስት አፍሪካ ክላድ›› በመባል የሚታወቀዉን ደግሞ ‹‹ክላድ 2 ወይም 2›› ብሎ መቀየሩን አሳዉቋል፡፡

በሳምንቱ ከሳይንቲስቶች ቡድን ጋር በተደረገ ዉይይት እና ስሞቹም ከየትኛዉም ‹‹የባህል፣ማህበራዊ፣ ብሄራዊ ፣ ክልላዊ፣ ስራ ወይም ከየትኛዉም ጎሳ ወይም ዘር ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸዉ እና በንግድ፣ ጉዞ፣ ቱሪዝም ወይም የእንስሳት ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ በማሰብ እዚህ ዉሳኔ ላይ እንደተደረሰ ተገልጿል፡፡

ሌሎች ብዙ በሽታዎች እንደ የጃፓን ኢንሲፋሊቲስ፣ ማርበርግ ቫይረስ፣ ስፓኒሽ ፍሉ እና ሚድል ኢስት ሪስፓራቶሪ ሲንድረም በሽታዎቹ ቅድሚያ ከተከሰቱበት ቦታ መነሻ በማድረግ የተሰየሙ ስያሜዎች ሲሆኑ፣የዓለም ጤና ድርጅት ግን እነዚህን ስሞች ለመቀየር ስለማሰቡ ምንም ይፋ ያደረገዉ ነገር የለም ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ነሐሴ 09 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *