የግንባታ ፈቃድ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን ሊሰጥ ነው፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የግንባታ ፈቃድ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን ለመስጠት በዕቅድ መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታዉቋል፡፡

ባለስልጣኑ በ2015 በጀት ዓመት በግንባታ ፈቃድ ዘርፍ የተቋሙን መሪ ዕቅድ መሰረት በማድረግ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጅ በማስደገፍ ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ነዉ የገለጸዉ፡፡

የባለስልጣኑ የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣በበጀት ዓመቱም በማዕከልና በክፍለ ከተማ የሚሰጡ አዲስ የግንባታ ፈቃድ፣ ፕላን ስምምነት፣ ማሻሻያ፣ የስም ለውጥ እና አገልግሎት ለውጥ ለሚፈልጉ ተገልጋዬች አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የህንጻ ህግጋትንና የከተማውን መዋቅራዊ ፕላን መሰረት ያደረገ፣ የግንባታ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት፤ ከማዕከል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር 38 ሺህ 200 የግንባታ ፈቃድ አገልግሎቶችን በኦን ላይን ለመስጠት በዕቅድ ተይዟል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቶቹም 15 ሺህ የፕላን ስምምነት፣ 5 ሺህ በተለያየ እርከን ለሚገነቡ ግንባታዎች አዲሰ የግንባታ ፈቃድ፣ 2 ሺህ 500 የግንባታ ማሻሻያ ፈቃድ፣ 2 ሺህ 200 ቀደም ብለው ለተገነቡ ህንጻዎች የግንባታ ፈቃድ እና ሌሎችም አገልግሎቶች ይገኙበታል ነዉ ያሉት፡፡

አገልግሎቱ በኦን ላይን መስጠት መጀመሩ የተገልጋዩችን እንግልትና ምልልስ በማስቀረት፣ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ከማስቀረቱ በተጨማሪ አገልግሎቱን ግልጽ በማድረግ ሙያው ተከብሮ እንዲሄድ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ነሐሴ 09 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.