ቻይና ሰብዓዊነትን የሚጣረስ ወንጀል ሳትፈጽም አትቀርም ብሏል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፡፡

የቻይና በአግላይነት እና በዘፈቀደ እስር ቤት ያስገባቻቸዉ የዩጉር ጎሳ ተወላጅ እና ሌሎች ሙስሊሞች ላይ ምናልባት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሳትፈጽም አልቀረችም ብሏል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት በቻይና ላይ ባላቸዉ የተለሳለሰ አቋም በብዙ ዲፕሎማቶች እና የመብት ተሟጋች ሲተቹ ቢቆዩም የአራት ዓመት የስራ ዘመናቸዉ ሊያበቃ ደቂቃዎች ሲቀሯቸዉ ሪፖርቱን ይፋ አድርገዋል፡፡

48 ገጽ ያለዉ ሪፖርቱ ቻይና በተከተለቻቸዉ የሽብር እና የጽንፈኝነት ምላሽ ስትራቴጂ ምክንያት በዢንጂያንግ ግዛት ዉስጥ ከባድ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ፈጽማለች ብሏል፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ እንደገለጸዉ በዩጉር ጎሳ ተወላጅ ሙስሊሞች እና በሌሎች የሙስሊም ማህበረሰቦች ላይ በዘፈቀደ በተፈጸመ እስር ምክንያት በቻይና መንግስት አለምዓቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል መፈጸሙን ገልጿል፡፡

ሚሼል ባችሌት የቻይና መንግስት እነዚህን በየካምፑ እንዲሁም በተለያየ የማቆያ ስፍራዎች የታሰሩ ሁሉንም ዜጎች እንዲፈታ አዘዋል፡፡

የተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ቻይናን በምታደርሰዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ሲወቅሱ ቆይተዋል፣ አሜሪካም ቻይናን በዘር ጭፍጭፋ ከሳታለች፡፡

ቻይና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣዉን ሪፖርት በፍጹም አልቀበልም ስትል 131 ገጽ ያለዉ ሪፖርት አስገብታለች፡፡

በጉዳዩ ላይ ብዙ ቁጥር ያላቸዉ ሙስሊሞች ቻይና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ታቁም በሚል ለተቃዉሞ አደባባይ መዉጣታቸዉን የዘገበዉ ሮይተርስ ነዉ፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.