የቅድመ ካንሰር የልየታ ምርመራ ዘመቻ ከነገ ጀምሮ ሊሰጥ ነዉ፡፡

የዓለም የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወርን ምክንያት በማድረግ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ እና የቅድመ ካንሰር የልየታ ምርመራ ዘመቻ ከመስከረም 21 ጀምሮ መሰጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡

የፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ማዕከል ለጡት ካንሰር ምርመራ አገልግሎት የሚዉለውን ማሞግራፊ የተሰኘ መሳሪያ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በአገር ውስጥ ተደራሽ የሆነ ህክምና መስጠት መጀመሩን ገልጿል፡፡

የማዕከሉ ባለቤትና መስራች አቶ ብሩክ ፍቃዱ ይህን አዲስ መሳሪያ በመጠቀም ከመስከረም 21 ጀምሮ እስከ ጥቅምት ለአንድ ወር የሚቆይ ሙሉ ምርመራ በማእከሉ ውስጥ በነፃ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የምርመራ ማሽን የሚደረግ የቅድመ ካንሰር ልየታ በ 3ዲ እይታ በመታገዝ ካንሰሩ ሳይስፋፋ እና ሳይሰራጭ እንዲሁም ምልክት ማሳየት ከመጀመሩ በፊት ህመሙን በአጭሩ ታክሞ መዳን ለማስቻል እንደሚጠቅምም ተገልጿል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በአገራችን ኢትዮጵያ በአሳሳቢነቱ በሁለተኛ ደረጃ በተቀመጠው የጡት ካንሰር ህመም ምክንያት በአመት ከ40 ሺህ በላይ ሴቶች ህይወታቸው እንደሚያልፍ ገልጸዋል፡፡
በተለይ እድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ሴቶች ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግን ልምድ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ማዕከል ህክምናውን አቅም ለሌላቸው እና ለተመረጡ መስሪያ ቤቶች በነፃ በመስጠት እንዲሁም ለመንግስት ሰራተኞች የ50 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ህክምናውን ሙሉ በሙሉ በሴቶች መስጠት መጀመራቸውን የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፍሬገነት ጌታቸው በመግለጫው አንስተዋል።

በቤዛዊት አራጌ
መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *