በአዲስ አበባ በትራፊክ አደጋ የሟቾች ቁጥር ጭማሪ ማሳየቱ ተገለፀ።

በትራፊክ አደጋ የሟቾች ቁጥር ጭማሪ ማሳየቱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገልጿል ።በ2014 በጀት አመት 411 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ማጣታቸውም ነው የተገለፀው።

ይህም ቁጥር ባለፈው አመት ከነበረው የሞት መጠን ጋር ሲነፃፀር በ6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የማኔጅመንቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በሚያስቀምጠዉ መስፈርት መሰረት ግን በመቶ ሺህ ህዝብ ምን ያህሉ ናቸዉ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ የሆኑት እንዲሁም በየአስር ሺህ ተሽከርካሪ ቁጥር ምን ያህል ሰዎች ናቸዉ እየሞቱ ያሉት የሚለዉን ከተመለከትን ደግሞ የተሻለ ዉጤት እያስመዘገብን ነዉ ሲሉ የገለጹት ደግሞ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ናቸዉ፡፡

ከዛሬ አስር አመታት በፊት በየአስር ሺህ ተሽከርካሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 136 እንደነበር ያነሱት ኢንስፔክተር አሰፋ አሁን ላይ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ 30፣ 40 አካባቢ ዝቅ ማለቱን አንስተዋል፡፡በአዲስ አበባም ይህ ቁጥር ወደ 11 ዝቅ ማለቱን ነዉ የገለጹት፡፡

ባለፈው አመት በትራፊክ አደጋ 389 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ መሆናቸዉን አንስተዉ በዚህ አመት ግን የ22 ተጨማሪ ሰዎችን ህይወት በመንጠቅ 411 ሰዎች ህይወታቸውን እንዲያጡ ማድረጉን ገልፀዋል ።

በተጨማሪም አምና ከነበረው የከባድ እና የቀላል አካል ጉዳት መጠንም መጨመሩ ነው የተገለፀው ። በዚህም ከባድ የአካል ጉዳት መጠን ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የ4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል ።

በከተማዋ ከደረሱ አደጋዎች መካከልም 80 በመቶ የሚሆነው በእግረኞች ላይ የደረሰ መሆኑም ተመላክቷል።በእስከዳር ግርማመስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *