የዩክሬኗ ዋና ከተማ ኬቭ በሚሳኤል ተመታች፡፡

በፍንዳታዉም ብዙዎች መሞታቸዉን እና ሌሎች ደግሞ መቁሰላቸዉ ተሰምቷል፡፡

ሩሲያ የወታደራዊ ዘመቻዋን በቀጠለችበት በዚህ ወቅት፣ በኬቭ እና በሌሎች የዩክሬን ከተሞች የተከሰተ ፍንዳታ ብዙዎችን ለሞት መዳረጉ ተገልጿል፡፡
ሩሲያን እና የክሬሚያን ሰርጥ የሚያገናኘዉ ድልድይን ኢላማ ያደረገ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ የተከሰተዉ ይህ ፍንዳታ፣ አጸፋዊ ምላሽ ሊሆን እንደሚችል የዩክሬን የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ገልጿል፡፡
ቢያንስ ወደ አራት አከባቢ የሚሆኑ ፍንዳታዎች መሰማታቸዉን የገለጸዉ ኬቭ ኢንዲፔንደንት በባቡር ጣቢያ አከባቢም ፍንዳታዎች እንደነበሩ ገልጿል፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፣ ሩሲያ ሀገራቸዉን ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት እየጣረች ነዉ ሲሉ ከሰዋል፡፡
የዩክሬኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዴኒስ ሺምይጋል በበኩላቸዉ በ8 ክልሎች ላይ 11 መሰረተ ልማቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

በዚህ ፍንዳታም አንዳንድ አከባቢዎች ግንኙነት መስመራቸዉ ሊቋረጥ ይችላል፤የመብራት፣ የዉሃ እና የግንኙነት መስመሮች ሊቋረጡ ስለሚችሉ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡
በፍንዳታዉም ቢያንስ አምስት ሰዎች ሲሞቱ 12 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ፖሊስ አስታዉቋል፡፡

እሁድ ዕለት የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በክሬሚያ ድልድይ ላይ የደረሰዉ ጉዳት በዩክሬን የደህንነት ሀይሎች የተፈጸመ የሽብር ጥቃት ነዉ ሲሉ ገልጸዉት ነበር፡፡
ዩክሬን ስለፍንዳታዉ ሀላፊነት ያልወሰደች ሲሆን ፣ የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ ማይካሂሎ ፖዶሊያክ በበኩላቸዉ ፍንዳታዉ ‹‹ ጅማሬ›› ነዉ ሲሉ በትዊተር ገጻቸዉ ላይ አስፍረዋል ሲል የዘገበዉ ፕሬስ ቲቪ ነዉ፡፡

በእስከዳር ግርማ

መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.