የኢፌዲሪ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከህገ-ወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 665 የባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን አስታዉቋል፡፡
በአገልግሎቱ የታገዱት የባንክ ሂሳቦቹ ህጋዊ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ በህገ-ወጥ መንገድ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ከሉ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር በህገ-ወጥ መንገድ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ናቸዉ፡፡
በወንጀል ድርጊቶቹ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በህግ ተጠያቂ የማድረግ የተጠናከረ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል።
የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም የተገኘን ሃብት ከህጋዊ ምንጭና በህጋዊ መንገድ የተገኘ በማስመሰል የመጠቀም ወንጀሎች አፈፃፀም በየጊዜው እየተቀያየረ ያለ ወንጀል ከመሆኑም ባሻገር፣ ከወንጀል ድርጊቶቹ የተገኘው ሃብት ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል መፈፀሚያ ጭምር የሚውል በመሆኑ የመከላከልና መቆጣጠር ስራው በተጠናከረ አግባብ በመከናወን ላይ ነዉ ብሏል አገልግሎቱ።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም











