“የተማረ ሰው መብቱን ይጠይቃል” በሚል አባባላቸው የሚታወቁት ብርጋዴር ጀነራል ታደሰ ብሩ 100ኛ አመት የልደት በዓላቸው ሊከበር ነው።

የኦሮሞ ህዝብ ለመብቱ እና ለነፃነቱ ትግል ባደረገበት ወቅት ትልቅ ቦታ የነበራቸው ብርጋዴር ጀነራል ታደሰ ብሩ 100ኛ አመት የልደት በዓላቸው ሊከበር መሆኑ ተገልጿል።

የኦሮሞ ህዝብ ትምህርት እንዲያገኝ እና ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን በሰሩት ታላቅ ስራ የሚታወቁት ብርጋዴር ጀነራል ታደሰ ብሩ “የተማረ ሰው መብቱን ይጠይቃል” በሚል አባባላቸው ይበልጥ ይታወቃሉ ሲሉ የገለፁት ጋዜጠኛ እና የማህበረሰብ አንቂ የሆኑት አቶ ደመቀ ነጋሳ ናቸው።

የብርጋዴር ጀነራል ታደሰ ብሩ ልጅ እና የብርጋዴር ጀነራል ታደሰ ብሩ ፋውንዴሽን መስራች የሆኑት ወይዘሮ ፀሀይ ታደሰ በበኩላቸው የልደት በዓሉ የሚከበረው በሁለት ምክንያቶች መሆኑን አንስተዋል ።
ይህም የዛሬው ትውልድ የእኚህን ታላቅ ሰው ስራ በተለይ በትምህርት ዙሪያ የሰሩትን ስራ እንዲያውቅ እንዲሁም ፋውንዴሽኑን ለመደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጥቅምት 13 ጀምሮ ለተከታታይ 8 ሳምንታት በአራት ፕሮግራሞች ተከፍሎ የሚከበር መሆኑንም አንስተዋል።

በወይዘሪት ዙፋን ዑርጋ “ከደናኔ እስከ ፊንፊኔ” በሚል ርዕስ በኦሮምኛ እና በአማርኛ የተፃፈ በብርጋዴር ጀነራሉ የህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መፅሐፍ ምርቃት ፤”ሁሉም ሰው ይማር” በሚል መሪ ቃል በ46 የኦሮሚያ ከተሞች የሩጫ ውድድር ፣ የጥያቄና መልስ እንዲሁም የብርጋዴር ጀነራሉን የህይወት ጉዞ በሚያስቃኝ የፎቶ አውደርዕይ ተከፍሎ የሚከበር መሆኑ ተገልጿል።

የመፅሐፉ አንድ ሚሊየን ኮፒ መታዘዛቸውን እና ዋጋውም 300 ብር መሆኑን ደራሲዋ ገልፀዋል።

በእስከዳር ግርማ
ጥቅምት 02 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *