በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም የተቋቋመው ወርኪንግ ግሩፕ፣ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ የመንግስት እና የግል የፋይናንስ ተቋማትን የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራው ነው ብሏል።
እስከ 2024 ዓ.ም ድረስ ይህንን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት ተቋሙ እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡
የግል ቢዝነስ ተቋማት ከመንግሰት የፋይናንስ ተቋማት ጋር ተሳስረው እንዲሰሩ እና ከብሔራዊ ባንክ የሚወጡ ፖሊሲዎች ለግል የፋይናንስ ሴክተሮች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም የዎርኪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ ክብረት ተናግረዋል።
አክለውም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሃብቶች ስለ ዲጅታል ፋይናንስ ጠቀሜታ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው እና ተሳታፊ እንዲሆኑ ወርኪንግ ግሩፑ ይደግፋልም ብለዋል።
በተጨማሪም የአቅም ግንባታ ስራን በማጎልበት የስራ እድል ለመፍጠር የመንግስት እና የግል የፋይናንስ ተቋማት በመናበብ እንዲሰሩ አጋጣሚዎችን እየፈጠረ እንደሚገኝም አቶ ዮሴፍ ገልፀዋል።
የዲጅታል ፋይናንስ ሰርቪስ ወርኪንግ ግሩፕ ከቻፓ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ጋር በመሆን 40 የፋይናንስ ተቋማትን ተሳታፊ የሚያደረግ ኤግዚቢሽ በሚቀጥለው ረቡዕ እና ሐሙስ በኢንተርኮንቲኔንታል ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታዉቋል፡፡
በመሳይ ገ/መድህን
ጥቅምት 03 ቀን 2015 ዓ.ም











