በሃገራችን የጡት ካንሰር በሽታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡

የጡት ካንሰር በሽታ አሁን ላይ በስፋት የተስፋፋ እና የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ ያለ በሽታ መሆኑን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

በሽታዉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በጡት እና በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ላይ የሚሰራዉ አለምጸሀይ የጡት ካንሰር ፋዉንዴሽን መስራች እና ዋና ዳይሬክተር ፍሬህይወት ደርሶ ናቸዉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም የተናገሩት፡፡

ችግሩ የተባባሰ ቢሆንም በበሽታዉ የተጠቁ ሴቶችን ቁጥር ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ፣ መረጃም በብዛት አለመሰብሰቡ እና በተለይ በገጠር የሚገኙ እናቶች እንደማይቆጠሩ እና ትክክለኛዉን አሀዛዊ መረጃ ለማግኘት ከባድ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በዚሁ በሽታ ምክንያት በርካታ ሰዎች በጡት ካንሰር እየሞቱ መሆናቸዉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ዙሪያ ትንሽ ግንዛቤ ቢኖርም በቂ ባለመሆኑ እናቶች ጉዳቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ እንደሚመጡ እና ለሞት እንደሚዳረጉም ገልጸዋል፡፡

በዚህ የጡት ካንሰር በሽታ የሚሞቱ ሴቶች አብዛኞቹ አቅም የሌላቸዉ መድሀኒት እና ህክምናዉን ማግኘት የማይችሉ መሆናቸዉንም ያነሳሉ፡፡
እነዚህን አቅመ ደካሞች ለመርዳት ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ የ5 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ለማድረግ ማሰባቸዉን እና በዕለቱም 5 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡

ባለፈዉ ዓመት በነበረዉ የእግር ጉዞ ከ 2 ሺህ ሰዉ በላይ መገኘቱን እና ወደ 2.5 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ብዙዎችንም መርዳት መቻሉን ነግረዉናል፡፡

ፋዉንዴሽኑ ከሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች ወደ ጥቁር አንበሳ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጡት ካንሰር እና በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ታመዉ ለሚመጡ ሴቶች ከሆስፒታሎቹ ጋር በጋራ በመሆን እስካሁን ከ 4ሺህ በላይ ታካሚዎችን ማሳከሙንም አክለዋል፡፡

ወደ ሆስፒታል መጥተዉ መታከም የማይችሉ፣የማይፈልጉ እና በሽታዉን የማያዉቁ እናቶችን በያሉበት እየሄዱ ለማከም በማሰብ፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እና ምርመራ ከ 2 ወራት ጊዜ በኋላ ለመጀመር መታሰቡንም አብራርተዋል፡፡
የ 5ኪሎ ሜትሩ የእግር ጉዞዉ ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድም ለማወቅ ችለናል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.