በአፍሪቃ ኅብረት መሪነት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሃት ልዑካን መካከል የተጀመረው የሰላም ውይይት ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

በውይይቱ ከሚሳተፉ ከሁለቱም ወገኖችም ሆነ ከአወያዮችም ሆነ በታዛቢነት ከተገኙት እስካሁን እሑድ ዕለት እንደሚጠናቀቅ ስለሚጠበቀው የሰላም ውይይት ሂደትም ሆነ ዐበይት የውይይት ነጥቦች በይፋ የተገለጠ ነገር የለም።

ሆኖም ምዕራባውያን ሃገራት በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ትግራይ ክልል የገባው ወታደራዊ ኃይሉ በጦር ግንባር የሚያደርገውን ግስጋሴ እንዲገታና የተኩስ አቁም እንዲያደርግ ግፊት እያሳደሩ ነው የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል።

የሀገር ውስጥ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙሃንም ይህንኑ የሚያመላክቱ ዘገባዎችን አቅርበዋል።

በዚህ መሀል ከሰዓታት በፊት በደቡብ አፍሪቃው የሰላም ውይይት እንደሚሳተፉ የተገለጸው የህወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻጻቸው «የኢትዮጵያ የሰላም ንግግር በጦር ሜዳ ላይ ባለው ሁኔታ ተጽዕኖ ሳያሳርፍበት አይቀርም» በሚል ዘ ኤኮኖሚስት የጻቸውን ዘገባ ተችተዋል።

ዘ ኤኮኖሚስት የመንግሥት ኃይሎች ወደ መቀሌ እየቀረቡ ነው የሚለውን ያልተረጋገጠ መረጃ የተቀበለ ይመስላል ያሉት የህወሃት ቃል አቀባይ በአሁኑ ሰዓት ትግራይ ክልል ውስጥ ውጊያ የሚካሄደው ከመቀሌ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው ኮረም እንደሆነም ጠቁመዋል።

የመቀሌ አውሮፕላንን በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ስለመሆኑ እየተየጠቁ መሆኑን በመግለጽም ትግራይ ክልል ውስጥ ተያዙ ስለሚባሉ ቦታዎች ተአማኒ መረጃ እየወጣ እንዳልሆነ በደፈናው ተችተዋል።

በአንድ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን እና ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን ቀናት የቀሩት ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲያበቃ የሰላም ውይይት እየተደረገ ቢሆንም ውጊያው እንዳልቆመ ነው የሚገለጸው።

እንዲህም ሆኖ በጦር ኃይል የሚፋለሙት ኃይሎች ሰላም ለማውረድ ወደ ውይይት ጠረጼዛ በይፋ መመለሳቸውን ብዙዎች አዎንታዊ ነው እያሉ ነው።

@DW

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.